‹‹የጠፈር ባይተዋሩ›› ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ <br> ክፍል አንድ <p align='right'><font size='2'>ብርሃነ መስቀል ደጀኔ</font></p>

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

‹‹የጠፈር ባይተዋሩ›› ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ
ክፍል አንድ

ብርሃነ መስቀል ደጀኔ

  


‹‹ሞት እንደሁ ልሙት፣ በሴኮንድ መቶኛ  
እንቅልፍ እንደሬሣ፣ ዘለዓለም ልተኛ፡፡ 
… መንገድ ስጡኝ ሰፊ ስሄድ እኖራለሁ 
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ 
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ፡፡ 
የሌለ እስቲፈጠር የሞተ እስቲነቃ 
 በትልቅ እርምጃ ከመሬት ጨረቃ
 ከጨረቃ ኮከብ 
 ካንዱ ዓለም ወዳንዱ 
ስጓዝ እፈጥናለሁ 
በፀሐይ ላይ ቤቴን ጎጆ እቀልሳለሁ፡፡
 . . . መንገድ ስጡኝ ሰፊ 
 ፀሐይ ልሁን ፀሐይ
 እንደ ጽርሐ አርያም ሁሉንም የሚያሳይ 
 እሳተ ገሞራ አመድ እረመጡን 
ጎርፍ የእሳት ጎርፍ ልሁን፡፡
 … መንገድ ስጡኝ ሰፊ›› 

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበረው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ የ‹‹ጠፈር ባይተዋር›› ሲል በ1961 ዓ.ም ከገጠመው እጅግ ‘ሮማንቲክ’ እና ጥልቅ የጠቢብ መንፈሱን ከሚገልጽለት ቅኔው የተወሰደ ነው፡፡ 

ለማስታወስ ያህል- ሠዓሊና ባለቅኔው ገብረክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ህዋ ላይ በተለይ ‹‹አብስትራክት›› የተሰኘውን ዘመናዊ የሥዕል አሠራር ስልት በስፋት ከማስተዋወቅ በላይ የሀገሪቱን እና የሕዝቧን ሕይወት /ባመዛኙ አጽም በአጽም በሆኑ ሥዕሎቹ በመግለጽ፣ የጠቢብና የዜግነት ገዴታውን በመሥዋዕትነት ጭምር የተወጣ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ 

ድንቅ ሥዕሎቹንም በሀገርና በውጭ ሀገር በግልና በቡድን በተደጋጋሚ ያሳየ ሲሆን፣ በሕዝቦች የባሕል ልውውጥም በየጊዜው የኢትዮጵያ የሥነጥበባት ቡድን መሪ ልዑክ በመሆንም በልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ አደባባዮች ላይ ሀገሩን የወከለ የጥበብ ሰው ነበር፡፡ ለቡድንና ለግል የሥዕል ኤግዚቢሽን ትርኢቶችም /አንዳንዶቹን በድጋሚ/ ጀርመን፣ ዩጎዝላቭያ፣ ግሪክ፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ቼኮዝላቫኪያ፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ብራዚል፣ ስፔን፣ ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅግ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ ወዘተ… ረጅም ጉዞ የፈፀመ ሲሆን፣ በዘመናዊ አሣሣል የጥበብ ስልቱ በሀገሩ ብኩርናን ከማግኘት አልፎ ለዓለም የሥነ ጥበባት ባሕልም አንድ የግሉና ልዩ የሆነ መለዮውን ያበረከተ፣ ሀገሩንና አህጉሪቱን ጭምር ያስጠራ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር፡፡ 

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ዕድገት አርአያ በመሆኑ በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት የሀገሪቱን ከፍተኛና ዓለም አቀፋዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት በአድናቆት የተቀበለው ሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ እንደ መምህርነቱም ከ1955 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ባሉት 12 ዓመታት ውስጥ ዛሬ ለሀገሪቱ አንቱ የተሰኙ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሠዓልያን አፍርቷል፡፡ ‹‹ሞዴል አርቲስትና መምህር›› በመሆኑም በ1963 እና 1964 ዓ.ም ከወቅቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒሰቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በ1969 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ለፈፀመው ታላቅ የማስተባበር ተግባርም ከዘመቻው መምሪያ የወርቅ ሜዳልያ ተሸልሟል፡፡

 በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ግጥም ባሕልም ውስጥ ገብረክርስቶስ ደስታ ራሱን የቻለ ሀተታ ነው፡፡ ገብረክርስቶስ በሕይወቱ ሳለ አንዳንድ ግጥሞቹ እና ቅኔዎቹ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ታትመው የወጡለት ሲሆን፣ አንዳንዶቹንም በልዩ ልዩ መድረኮች በሀገር እና በውጭ ሀገር ጭምር ራሱ አንቧቸዋል፡፡ እንደዘመናዊ ሥዕሎቹ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ የሥነግጥም ባህልም ውስጥ ገብረክርስቶስ ሀዲስ ዘር የዘራ የሀገራችን ዘመናዊ ግጥም ቆርቋሪ ነበር፡፡ ግጥሞቹ/ ቅኔዎቹ/ በሀዲስና በእንግድነታቸው ከጥቂቶቹ ተቃውሞ ቢያተርፍበትም በብዙዎቹ አድናቂዎቹ ተፈቃሪ ነበሩ፡፡

 ገብረክርስቶስ ደስታ ወደ 60 ያህል የሚጠጉ ግጥምና ቅኔዎቹን ትቶልን አልፏል፡፡ ግለኛና አዳዲስ የአሰነኛኘት ዘዴ በመከተል በኢትዮጵያ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ አዲስ ንቅናቄ የፈጠሩ ግጥሞቹ እና ቅኔዎቹ የአማርኛ ቋንቋን ጣዕምና ለዛ ግልጽና ቀላል በሆነ፣ ነገር ግን ቅኔያዊ ውበትን በተጎናፀፈ የገለጻ ኃይል እስከ ባህላዊው ትውፊታችን ድረስ በመዝለቅ የኢትዮጵያውያንን ‹ነፍስ› የገለፁ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን መልክአ ምድራዊ ገጽታ ከመቅረፃቸውም በላይ፣ ለሀገሩ ባህለኛነቱንና ወገን ወዳድነቱን ባጠቃላይ- ኢትዮጵያዊ ስብእናውን አሟልተው የገለጹለት ናቸው፡፡

 ከቀደምቱ የ‹‹እማ ኢትዮጵያ አርመኛ ባለቅኔዎች›› ከነዮፍታሔ ንጉሤ፣ ከእነ ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ እና ከነዮሐንስ አድማሱ ‹‹መዝሙረ ኢትዮጵያ›› ቅኔዎች በአርአያነቷ አቻ የምትሆነው የገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹ሀገሬ›› /1951 ዓ.ም/ ዛሬ ያለምንም ማዳነቅ የብዙዎቹ ፍቁረ ኢትዮጵያውያን የነፃነት ሴማ ነች፡፡ እንኳን በሕይወት ካሉት፣ በሕይወት ከተለዩን መሀል እውቁ የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁሩና ሀያሲ ሥዩም ወልዴ፣ እውቁ የሥነ-ብዕል ሊቅ ዶ/ር እሸቱ ጮሌ ወዘተ. . . ዛሬም በዐፀደ ነፍስ ሆነው/ በሕይወት ሳሉ እንደሚያደርጉት/ ‹‹ሀገሬ››ን በአርምሞ የሚያዜሟት ይመስለኛል፡፡

 አብዛኛው የጥበብ ቤተሰብ በቅርብ እንደሚያውቀው በዚህች ሀገር የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ወሰጥ አንዳች አሻራ ጥሎ ያለፈው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ በተለይ ካለፈው አንድ አሠርት ዕድሜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን መድረኮች ሲወሳ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

 በሕይወት ያለፈው ገብረክርስቶስ ደስታ ከነበሩን ብርቅዬ የጥበብ ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ ይሁንና በዘመነ ደርግ፣ በሕይወቱ ላይ ባንዣበበ አደጋ በመስከረም ወር 1971  ዓ.ም ሀገሩን በስደት ጥሎ እንደወጣ ቀረ፡፡ ከተሰደደ ከሁለት ዓመታት እንግልት በኋላ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም. በተወለደ በ49 ዓመቱ አሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ሕይወቱ አለፈች፡፡ በወቅቱ አስከሬኑ ጭምር ‹ሀገር የከዳ› ተብሎ ለሀገሩ መሬት ሳይታደል ግብዓቱ መሬቱም እዚያው ተፈፀመ፡፡ 

ይህን የሕይወቱን ትራዤዲያዊ ፍፃሜ አስመልክቶ ዛሬ በሕይወት የሌሉትና ተቆርቋሪው የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁር ሥዩም ወልዴ ‹‹የሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ግጥሞች ››/1981ዓ.ም / በሚለው ዝክረ ጽሑፋቸው እንዲህ ደምድመውታል፡፡ 

. . . የገብረክርስቶስ ሞት ተራ የአካል ሞት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሞቱን ትራዤዲያዊ የሚያደርገው አንድ ቁም ነገር በግጥሞቹ ውስጥ እናገኛለን፡፡ . . . በተለያዩ ግጥሞቹ ውስጥ ተመልሶ እስኪረግጣት የሚናፍቃት፣ እኔም ከእናንተ ይበልጥ የምታኮራ አገር አለችኝ የሚላት፣ ሰው ከአገሩ ውጭ ሰው አይደለም ብሎ ሲተማመንባት የነበረች አገሩ፣ የሕይወቱን የመጨረሻ ሕልፈት ሳታስተናግድለት መቅረቷ ነው፡፡ እንኳን ሞቶ አስከሬኑን፣ ግድ ካልሆነበት ቀፅበታዊ ትንፋሹን እንኳን በ‹‹ባዕድ ሀገር›› መተንፈስ የማይፈልገው ገብረክርስቶስ በ1973 በኦክላሆማ ስቴት ማረፉ የሰውን ልጅ ሕይወት ወሳኝ ወቅት ጣጣ የሚያስታውስ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፡፡ …

በሕይወት ካሉትም መሀል-ዛሬ በአሜሪካ /ሜኔሶታ/ ነዋሪ የሆነው፣ ዘመነኛው እና እጅግ አድናቂ የጥበብ ባልንጀራው የ‹‹ልጅነት›› እና የ‹‹ወለሎ ወለሎታት›› ባለቅኔ ሰለሞን ደሬሣ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ሀገር ቤት መጥቶ በነበረ ጊዜ ለ ‹‹ሪፖርተር›› መጽሔት /ቅጽ2 ቁ. 13 መስከረም 1991 ዓ.ም/ ስለዚሁ ስለገብረክርስቶስ የመጨረሻ እጣ የገለፀው እንኳን የወዳጆቹን የማንኛውምንም ሰው ልብ የሚሰብር ነው፡፡ 

. . .ለኢትዮጵያውያን ፀሐፊዎችና ሠዓሊዎች ችግር ይደርስባቸዋል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ደረሰበት፤ መጨረሻው ላይ ስለ አወጣጡ የሰማሁት ነገር አለ፡፡ እሱን አላጣራሁምና አልደግመውም፡፡ ችግር ደርሶበት ወጥቶ ታሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አንድም ኢትዮጵያዊ በሌለበት ማንም በማያውቀው ሀገር ኦክላሆማ በተባለ ቦታ ሞተ፡፡ አሜሪካ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ እኔ ያለሁት ሜኔሶታ እሱ ያለው ኦክሎሆማ ነበር፡፡ ብሰማና ባውቅ ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ ሲሞት የሚያውቀው ፊት እያየ ይሞት ነበር፡፡ አሁን ሳስታውሰው በጣም ሆዴን ይበላኛል፡፡

. . . ስለ ገብረክርስቶስ ‹‹አሌፍ››አዊ በሆነው በግሌ ትውስታ መጀመር ካለብኝ፣ ገብረክርስቶስን የማውቀው በርቀት እንጂ በቅርበት አልነበረም፡፡ ይኸም ዕውቂያዬ የሚጀምረው፣ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ ከ1957 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በዚሁ ግቢ ውስጥ ስለሚገኝ፣ በዚያች ጥቁር ሬኖ መኪናው ለምጽ ህብረ መልክ ከሰጠው ገጽታው ጋር ሲከንፍ እንድ ብርቅ የምናየው ሰው ነበር፡፡ ያ ልዩ ገጽታ የነበረው የሥዕል አስተማሪ፣ በዕረፍት ሰዓት በተማሪዎቹ በፍቅር ተከቦ በተመስጦ ሲደመጥ፣ ሲያወራ፣ ሲጫወት. . . በሩቅና በየአጥሩ ጥግ የምናየው አስገራሚ ትርኢት አሁን ድረስ ይታወሰኛል፡፡ ይህ ሩቅና የአካል እውቂያ፣ ለስድስትና ለሰባት ዓመታት የዘለቀ ድግግሞሽ ሲሆን፣ ደማቁም የልጅነት ትዝታዬ ነው፡፡ 

 ገብረ ክርስቶስን ያወቅሁት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነው፡፡ ‹‹መነሻ ለሥዕል›› ‹‹የሙዚቃ ድምፅ›› ‹ባለክራር›› ‹‹ከበሮ›› ወዘተ. . . የተሰኙትን ግጥሞቹን በሟቹ ወንድሜ በአድማሱ ኢሳይያስ /1946-1969 ዓ.ም/ ባለውለታነት ተዋወቅሁ፡፡ በተለይ ‹‹መነሻ ለሥዕል›› ዛሬ ውስጥ ለጨነገፈ የሠዓሊነት ዝንባሌዬ ያኔ ግን‹‹ለሮማንቲዝም››ጥበብ የጋለ ስሜቴ ቃለ መዝሙር ነበረች፡፡ 

አያልቅም ይህ ጉዞ ማስመሰል-መተርጎም 
በቀለም መዋኘት 
በመሥመር መጫወት 
ከብርሃን መጋጨት
 ለማወቅ ለመፍጠር/ ባዶ ቦታ መግባት፡፡ 
መፈለግ. . .መፈለግ… 
አዲስ ነገር መፈጠር 
ከማይታየው ጋር ሄዶ መነጋገር፡፡
 ሕይወትን መጠየቅ 
ሃሳብን መጠየቅ 
 ዓለምን መጠየቅ
 መሄድ መሄድ መሄድ 
መጓዝ ወደ ሌላ - ባዶ ቦታ መግባት
 በሃሳብ መደበቅ 
መፈለግ ማስገኘት፡፡ 
አያልቅም ይህ ጉዞ. . . 

የካቲት 66 ከነጓዙ መጣ፡፡ ‹‹ዕድገት በሕብረት›› … እና በመሀል የነበረው ጊዜ ገደበን፡፡ ርቀትን በቅርበት የተካልኝ አንድ አጋጣሚ ብቻ ቢኖር፣ ለሀገሩ ስንብት የመጨረሻ የሆነውን ‹‹አጠቃላይ የሥዕል ትርኢት›› /1969/ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህል አዳራሽ ሲያሳይ ነበር፡፡ ኋላ ወቅትም አልፈቀደ . . . አጋጣሚም አላገኘንም- የእርሱም መጨረሻ በመስከረም 1971 በስደት አከተመ፡፡ ሕይወቱም በትራዤዲ የመጠናቀቁን አሳዛኝ መርዶ የሰማሁት እጅግ ሰንብቶ ነው፡፡

 ቢሆንም፣ ገብረክርስቶስ በ‹‹ሞቱ ሕያው›› ሆኖ ወዲያውኑ መኖር ሲጀምር ለማየት ከበቁትም አንዱ ነኝ፡፡ ለዚሁ መንፈሱ የመጀመሪያው ወካይ አጋጣሚዬ፣ የአዲስ አበባው የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የቀለም ቅብ መምህር የነበረው ባንጀራዬ ሠዓሊ ፍፁም አድማሴ ነው፡፡ የፍፁሜ ስቱዲዮ፣ የቀድሞው የገብረክርስቶስ ደስታ ስቱዲዮ ነበረች፡፡ በየሳምንቱ አጋጣሚዬ፣ ገና ስቱዲዮው ስገባ፣ የፍፁም ምስለ ገብረክርስቶስ /‹‹ ፖርትሬት›/ ነበር የሚቀበለኝ፡፡ የሠዓሊና የቀለም ቀብ መምህር የሠዓሊ ጌቱ ሽፈራው ምስለ ገብረክርስቶስም ዓመታት /1975-1976/ ተቆጥረው የማያልቁ ውድ ወራት ነበሩ፤ ስለገብረክርስቶስ ለማውሳት ሰፊ ዕድል ሰጥተውኛል፡፡ የገብረክርስቶስ ‹‹ሞዴል›› ስብእናም፣ በፍፁሜ ሠዓሊነት፣ ገጣሚነት እና መምህርነት ወዘተ. . . ራሱን ሲገልጽም በእውን ለማየት በቅቻለሁ፡፡ / ነገር ነገር ያነሳዋል ከሆነ ይኸንኑ የገብረክርስቶስ የገጣሚነት እና የሠዓሊነት ተዋህዶ ሰብእና ‹‹ሞዴል››ነት በሠዓሊና ገጣምያኑ በእሸቱ ጥሩነህ፣ በቀለ መኮንን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ መስፍን ሀብተማርያም ክሱት ሆኖ ያየሁት ሲሆን ከዘለቁበትም ሠዓልያኑ ጀማል ካሣ፣ ጌቱ ተክሌ፣ ተስፋዬ ገብሬ፣ ሲሳይ ሽመልስ፣ ወጋየሁ አየለ፣ አገኘሁ አዳነ ወዘተ. . . የዚሁ ‹‹ተፅዕኖ›› ባለቤት ናቸው፡፡ 

እና የፍፁሜ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ጀርመን ጉዞ ስለገብረክርስቶስ ሌላ ውድ አጋጣሚ ተክቶልኛል፡፡ ገብሬ ለመጨረሻ ጊዜ ለሦስት ዓመታት የሠራበት /1969-1971/ እና ምናልባትም እንደመጀመሪያው ብሔራዊ ጋለፊ ሊቆጠር የሚችለው የአዲስ አበባው ማዘጋጃ ቤት የባህል አዳራሽ ስቱዲዮ ቤተኛ የመሆን ዕድል አጋጠመኝ፡፡ ሠዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀበተማርያም፣ የስቱዲዮው ተረካቢ ብቻ ሳይሆን፣ የገብረክርስቶስ ደስታ የመፈስ ሀብታት ጎተራ መሆኑ የላቀ ዕድሌ ሆነ፡፡ በተጨማሪ የባህል አዳራሹ ዕውቅ ተዋንያን ሥዩም ተፈራ፣ ሱራፌል ጋሻው፣ አልአዛር ሳሙኤል ወዘተ… የገብረክርስቶስ ረሀብ ጥማቴ-ምሉዕ ሕብስትና ጽዋ ሆኑ፡፡ ኋላ ጋሽ ስብሐት፣ ባሴ ሀብቴ፣ ደምሴ ጽጌ፣ ነቢይ መኮንን፣… ገብረክርስቶስ እንደጠቢብ ርዕሰ ነገሬ እንዲሆን የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በኋላም የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁሩ የሥዩም ወልዴ፣ የተማሪዎቹና የዛሬዎቹ አንጋፋ ሠዓልያን የእነ እሸቱ ጥሩነህ፣ የነ ታደሰ መስፍን ወዘተ… ዕውቂያ የበለፀገ ነገር አስገኝቶልኛል፡፡ ይህ ሁሉ ተባብሮ ከርቀት - ወይ ቤተሰብ ቤተኛነት ብሎም የትውስታው ዘካሪ ከመሆንም እንደ እድል ወደ ሕይወት ታሪኩ ምርመራና ጥናት አድርሶኛል፡፡ 

ገብረክርስቶስ ደስታ የቤተክህነት ሊቅ ከሆኑት፣ ከአለቃ ደስታ ነገዎ /1849-1947/ እና ከወ/ሮ ፀጸደማርያም ወንድማገኘሁ ጥቅምት 5 ቀን 1924 ዓ.ም በሐረር ከተማ ተወለደ፡፡ ለወላጆቹ በስተርጅና የተገኘ የመጨረሻና 10ኛ ልጅ ነበር፡፡ እናቱ የሞቱት ገና የመንፈቅ ልጅ ሳለ ነው፡፡

 የገብረክርስቶስ የጨቅላነት ጊዜ የተተካው በልጅነት እድሜ አበሳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የሦስት ዓመት ሕፃን ሳለ ነበር … ፋሺስት ኢጣሊያ በሐረር በወልወል ግጭት ሰበብ የመጀመሪያውን ወረራ የፈጸመ፡፡ በዚህም የልጅነት ዕድሜውን በስደት ጀመረው፡፡ በ1927 ከሐረር አዲስ አበባ፡፡ ሕፃኑ ገብረክርስቶስ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አዲስ አበባና ሕዝቧ በፋሽስት ሲፈጁ እዚሁ ነበር፡፡ ከልጅነት መሪር ትዝታዎቹ አንደ እናት ሆነው ካሳደጉት አባቱ መለያየቱ፣ የአባቱ በጣሊያኖች መታሠርና መጋዝ፣ ከእሥራታቸው ሲፈቱ ወደ ሐረር መመለሱ፣ ፋሺስቶቹም የሀገሬውን ልጅ ለዓላማቸው መኮተኮቻ እንዲሆን በከፈቱት ‹‹ቢላላ›› ትምህርት ቤት ከአባቱ ጉያ ተነጥቆ እንዲገባ መገደዱ ወዘተ… ዋነኞቹ ናቸው፡፡

 ኋላ በጉልምስና እድሜው ላይ ይጻፈው እንጂ ‹‹የደም ቀን›› /1959/ የሚለው የፀረ ፋሺስት ትውስታ ግጥሙ በቀጥታ ለየካቲት 12ቱ ሰማዕታትና ለልጅነት መራር ተዝብቱ ማካተቻ ነው፡፡ 

የገብረክርስቶስ ልጅነት- መራርም ሆነ ደማቅ ትውስታ የተተካው፣ ከነፃነት በኋላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረሩ የራስ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቆ /1933-1938/ ለቀጣይ ትምህርቱ አዲስ አበባ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ያለው ነው፡፡ መቼ እንደጻፋት አትታወቅ እንጂ፣ ‹‹ትዝታ›› የምትለው ግጥሙ፣ ይህንኑ የልጅነት ሕይወት ትዝብቶቹን የከተበችና ምናልባትም የጉልምስና ዘመኑ ስብእና መቅድማዊ መዝገቡ መሆኗን አለጥርጣሬ መቀበል ይቻላል፡፡ 

እና ይህች ቀዳሚቱ ክት ልጅነቱ፣ ጉልህና ደማቅ ሆኖ ለተገለጠ ለኋላ የጉልምስና ስብእናው ዓይነተኛዋ ምንጭ ሳትሆን አልቀረችም፡፡ እንደእኔ አመኔታ፣ ሦስቱ የሰብእናው ሕቱም ባሕርያት- የገብረክርስቶስ ሠዓሊነት፣ የገብረክርስቶስ ገጣሚና ባለቅኔነት እና የገብረክርስቶስ ብሔረተኛነት - ከዚሁ ከልጅነት ማደጎው ጥልቅ ሚስጢር የተቀዱ ናቸው፡፡ ሥዕል ‹እናቱ›፣ ግጥምና ቅኔ ‹‹አባቱ› የሆኑት ገብረክርስቶስ፣ በሁለቱ ተዋህዶ ገናን ብሔረተኛ የመሆኑ ምሥጢር ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡

 አንድም፣ የገብርክርስቶስን ክት የልጅነት ሕይወት፣ በሕይወቱ ‹ታላቅ ሰው› አድርጎ ከሚቆጥራቸው አባቱ ጋር አቆራኝቶ ማየትም ይቻላል፡፡ የሥዕልና የቅኔ ፍላጎቱን ከመኮትኮትና ከማዳበር ሌላ፣ የልጅነት አቅሙ በሚፈቅደውም መጠን፣ ስለ ሀገራችን ሊቃውንት፣ የጥበብ ሰዎችና የታሪክ ሰዎች ይተርኩለት እንደነበር ቤተሰቡ ይናገራል፡፡ ከአባቱ ጋር አደባባይ በሚወጣበትም ጊዜ ከየአዛውንቱ ጋር ያደርጉት የነበረውን ቁም ነገራም ውይይት ሁሉ፣ ልቦናውን ሰጥቶና ጆሮውን አቅንቶም ያዳምጥ ነበር፡፡ ጥቃት የማይወዱት፣ እጅግ ርህሩህና ቅን የነበሩት አባቱ፣ ለተቸገረ የሚያደርጉትን ብፅአት ገብረክርስቶስ ያስተውል ነበር፡፡ ኋላ ለተቸገረ አዛኝ፣ ድሃ-ወዳድ፣ ቸርና ለጋስ የነበረውን ገብረክርስቶስን ይህንን እና ይህን የመሳሰለው ሁሉ ገና በልጅነቱ -አንደበቱን በጥዑም ቃለ መዝሙር፣ ግጥምና ቅኔ፣ ልቦናውንና እጁን በቀለም በሥዕል ህሊናውንም በሀገር ታሪክና በዕውቀት ብሎም ጥልቅ በሆነ የወገን ፍቅር-የከተበው ይኸው ከአባቱ ጋር የነበረው ቅርብና ምሥላዊ ቁርኝት ነው፡፡ 

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በገብረክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ብርቱ ተፅዕኖ ያላቸው እኚህ አባቱ በ1947 ዓ.ም መስከረም 21 ያረፉ ሲሆን፣ የጥልቅ ቅኔዎቹ ቁንጮ ሊሆን በሚችለው ‹እረፍት አርግ አሁን› /1958/ በሚለው የግጥም ዝክሩ፣ ስብእናቸውን በጉልህ ቀርፆልናል፡፡ ትውስታውን ለእርሳቸው ያስፍረው እንጂ ዛሬ ‹መታሰቢያነቱ› ጭምር በኢትዮጵያ ሥነ ጥበባት መድረክ ላይ ‹የሕይወት ሩጫውን› ለጨረሰ ለራሱ ለገብረክርስቶስም እንደትንቢት ሆኖ እንደገዛ ራስ ኑዛዜው ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡ ‹እረፍት አርግ አሁን› . . . ለራሱ ለገብረክርስቶስ ሊባል ይችላል፡፡ሪፖርተር መጽሔት፤ጥቅምት 1993 ዓ.ም
 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethioreaders.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Sisay [1871 days ago.]
 His father was also great!

ናቫ [1870 days ago.]
 ከዚህ ትልቅ ሰው የስእልና የግጥም ስራዎቹ ባሻገር፣ ከሕይወት ታሪኩም ብዙ መማር ይቻላል።

Meseret [1130 days ago.]
 it is so nice

Aytenew [1085 days ago.]
 the who puts the non-erasable efforts to HIS COUNTRY

Estayih Animawu [1067 days ago.]
 This is very good reading!!!

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com