“ምርኮኛ” <br><i>ደራሲ ከቆንጂት ብርሃኑ</i>

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

“ምርኮኛ”
ደራሲ ከቆንጂት ብርሃኑ

  


"ምርኮኛ " የሚለውን መጽሐፍ አንብቤ በትዝታ ውስጥ ተዘፍቄ እገኛለሁ ። በእንባ እየተሞሉ የሚያስቸግሩኝን ዓይኖቼ ወረቀቱን ማየት እንኳ ባይችሉ ይህንን ጽሁፍ ጀመርኩት ። ልቤ መጽሐፉን እንደገና ለማየት ይፈራል ። ትቼው አርፌ የተቀመጥኩትን ትዝታ ቀስቅሶ አደራ እንደበላ ሰው ራሴን ያስወቅሰኛል ። ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በትዝታ ያነሆልለኛል ። በየጢሻው የተጣሉት ያልተቀበሩት ጓደኞቻችን ትዝ ይሉኛል ።በቀይ ሽብር ወቅት
በአገራቸው ተሰደው በገንዘብ እጥረት ይሆን ከፍተኛ በሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት ወይም ሞተዋል ተብሎ ቤተሰብ ስለተረዳ ወደ ትውልድ ሥፍራቸውን መመለስ አፍረው የሚኖሩት አንድ ጊዜ አሰብኳቸው ። በተወለዱበት ሃገር በስደት በድብቅ
መኖር ምን ያህል ያስከፋል ።

- ከበደሌና ከመቱ መካካል የልጁን ጡጦ በካልሲው ሸፍኖ ሚስቱን ከኋላ አስከትሎ ወደ ገበያ ሲኳትን ያገኘሁት የኢሕአፓ ልጅ ትዝ አለኝ ።በጣም ቸኩዬ ስለነበር ትንሽ ነበር ያጫወትኩት። ቢሆንም በመከራ ለምንኖር ሰዎች በቂ ነበር ። ምነው ቀኑ ሞልቶልኝ ሳወራው ባድር ኖሮ ። ቢሆንም ማስታወሻ ላይ በወቅቱ የከተብኩት እንዲህ ይላል ፡

" አካባቢን መምሰል ጥሩ ነው ይባላል ። ይህ አባባል ሁሉ ጊዜ ትክክል አይደለም ። አንዳንዴ አካባቢ ሞኝ ሊሆን  ይችላል ። አካባቢን መምሰልም ሞኝነት የሚሆንበት ጊዜም ይኖራል "

- በጋምቤላና በጎሬ መካከል ያገኘሁት የአዲስ አበባ ልጅ ምን ደርሶ ይሆን ? የጓሮ ጫት እርሻ ጀምሮ ነበር ።አሁንም ጫት እየቃመ ልጆችን ያሳድግ ይሆን?ልጆቹሽ ?ለትንሽ ደቂቃ አብሬው በነበርኩበት ወቅት ከዓይኑ ላይ ያነበብኩት ብቸኝነቱና ፣በሰቆቃ የተሞላው የድኩላ ኑሮው ትዝ አለኝ ። ደርግ ሲወርድ ምን ያህል እፎይታ አግኝቶ ይሆን ? ኢሊባቡር ሞቻ ያገኘሀኋቸው የድጎማ መምህራን ትዝ አሉኝ ። በበቃ የቡና ለቃሚዎች አለቃ የሆነው ትዝ አለኝ ። ቶባ ላይ ያገኘኋት ቆንጆ ልጅ ትዝ አለችኝ ። ታሪኳን በጽሁፍ ስላስቀመጥኩት ቀኑን ጠብቆ ለንባብ ይበቃል ።

የራሴን ታሪክ የማነብ ይመስል ብዙ ብዙ ትዝታ ቆንጅት ብርሃኑ ምርኮኛ በሚለው መጽሐፏ ጭራብኝ ሄደች ።ለዚህ ሁሉ ትዝታ ያደረሰችኝን ምን ብዬ ልርገማት?

እንደገና ሌላ መጽሐፍ ያስጀምራትና እንደበጠበጠችን ይበጥብጣት ፣ በትዝታ እንደወሰደችኝ እንደገና ይውሰዳት ፣ብዕሯን እንዲያበራለት በሃሳብ ያሰቃያት ፣ምርኮኛ እያጓጓኝ ተጀምሮ እንዳለቀ ሌላም ትጽፍና ማለቂው ቀን ያጓጓት!፣እንቅልፍ እንደነሳችኝ ጠረቤዛዋ ላይ ቁጭ ብላ ስትጽፍ ያሳድራት።

ለአንድ ደራሲ ይህ ምራቃት እንደሆን እንጂ እርግማን ይሆን ይሆን ?

"ምርኮኛ"ቆንጅት ብርሃኑ በ2002ዓ.ም.ሁሉም በዚህ ጽሁፍ ላይ ያለው አቆጣጠር የኢትዮጵያውያን ነው ለንብብ ያበቃችው ውብና ድንቅ መጽሐፍ ነው ።

"ምርኮኛ " በሁለት ትውልዶች መካከል የደረሰውን የመከራ ዘመን የሚያስረዳ ነው ። በቀይሽብር ያለቀው ትውልድ ሳይበቃ በኤድስ የተደገመው ወጣት ደግሞ ብዙ ነው ። የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕሪ ፍሬ ሕይወት ከቀይ ሽብር በቁስለኝነት አምልጣ በኤድስ ኤች.አይ ቪሕይወቷን ከማጣቷ በፊት በጽሁፍ የተወችው የሕይወት ታሪኳ ነው ። ታሪኳ እሷ በውስጧ ያለፈችበትን እውነተኛ ፍላጎትን የሚያንፀባርቅና ያለፈበትን ሰቆቃ ደግሞ ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነው ።

ፍርዬ የሁለት ጦርነቶች ምርኮኛ ሆና አገኘኋት እናም ለጽሑፏ ርዕስ እንዲሆን ወሰንኩ ። ፍርዬ ጅግና ነች ፣ በአንደኛው ጦርነት ቁስለኛ ሆና ቆየች ፣ ሁለተኛው ጦርነት ግን ሕይወቷ ነጠቃት ።ፍርዬ ዛሬም ጀግና ነች፣ ወደመጨረሻ የጻፈቻቸውን አንዳንዶቹን ገፆች መቼ እንደጻፈቻቸው ሳስብ ጥንካሬዋን አደንቃለሁ ። በጣም ሙንጭርጭር ያለ ስለሆነ ምንአልባት ከሞት ጋር እየታገለች በስቃይዋ መሀል እንደጻፈችው እገምታለሁ ።

          ምርኮኛ ገጽ 26

በዚህ መጽሐፍ ስለ ፍሬ ሕይወት ይተረክ እንጂ በአንድ አካባቢ ይደርግ የነበረውን የኢሕአፓ የወጣት ክንፍ ኢሕአወሊ እንቅስቃሴ ጉልህ አድርጎ ያሳየናል ። የፍሬ ሕይወት እናት ከሌላው የመጽሐፉ ገጸ ባሕሪ ከበላይሁን እናት አባት ጋር
ለልጆቻቸው የሚደርጉትን ድጋፍ ቁልጭ ብሎ ቀርቧል ። በችግርም ይሁን በደስታ ያልተለያዩት እነዚህ ሁለት ቤተሰቦች የመከራን ሬት አብረው ጠጥተዋል ። ፍሬ ሕይወት አናጢ የነበሩት አባቷ ከሞቱ በኋላ በችግር ከእናቷ፣ ሚሚ ከምትባል 
እህቷና ቃለአብና ሮቤል ከሚባለው ወንድሞቿ ጋር ነበር የምትኖረው ። በላይሁን ጎረቤታቸው ሲሆን ከእናትና አባቱ ጋር ነበር የሚኖረው ። የተለያዩ ገጸ ባሕሪያት ተጠቅሰዋል  አንተነህ ፣ ለምለም ፣ሄዋን ፣ ቅዱስ፣ ጋዲሳ፣አሰቻለው፣ዘርዓይ ፣ዳኙ፣ ታሪኩ፣ አመለ ፤ አስቴር፣ ድንቅነሽ ፣ ዘውዱ ፣እመቤት፣ ፈቃደ፣ ሚስጥረ ፤ ታረቀኝ
፣ፈቃደ ፣ ታደለ ፤ እንዲሁም ሌሎችም መጽሐፉ ውስጥ ይጠቀሳሉ ።

ይህ መጽሐፍ በልብ ወለድ መልክ ይፃፍ እንጂ እውነተኛ የሆነ ታሪካዊ ትረካ ነው ብል ማጋነን አይሆንም ። የዓላማ ጽናትን ፣ ፍቅርን ፣ መስዋዕትነትን ፣ ጓደኝነትን ፣ ለሃገር መሞትን ፣ ጨካኝነትን ፣ ከሃዲነትን የሚንጸባርቁ ልዩ ልዩ ገጸበሕሪያት ያሏቸውን ግለሰቦች በየአንዳንዱ ገጽ ውስጥ አካትቷል ።

ያ ትውልድ ለምን ታገለ ?ለምንድን ነበር የተሰዋው ?ስቃዩስ ለምንድነው ?ምን ዓይነት ግፍ ደርሶበታል ?ትውልዱን ከቀይ ሽብር በኋላ ምን ጠበቀው ? ይህንንና ሌሎች ጥያቄዎችን መልስ ለማግኘት ይህንን መጽሐፍ ማንበብ ይረዳል ። ዛሬ የዛን ትውልድ ታሪክ ለመበከል የተነሱትን " ምርኮኛ " እውነቱን በማሳየት፣በትረካ መልክ ለዓላማ የሞቱትን ዳግም ለመግደል የሚነሳሱትን ይሟገታል ።

ይህ መጽሐፍ ወቅቱ በመርዘሙ ምክንያት ከተረሳው " የእድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ " ወቅት ነው የሚጀምረው ። " እድገት በሕብረት" ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በወቅቱ ከአሥረኛ ከፍል በላይ የሆኑትን ተማሪዎች
ወደ ገጠር ዘምተው ገበሬውን እንዲያደራጁ ፣ እንዲያስተምሩ የታወጀ አዋጅ ነበር ። በዚህ መጽሐፍ ይህንን ዘመቻ በተመለከተ የነበረው ተቃውሞና ድጋፍ በመጠኑም ቢሆን ተጠቅሷል ። ይህ ዘመቻን በሚመለከት እስከ አሁን ብዙ ያልተፃፈለት ሲሆን የነበረውን ሁኔታ ሳትጨምር ሳትቀንስ ቆንጅት አስቀምጣዋለች ። ዋናዋ ገጸ ባሕሪ ፍሬ ሕይወት በቤተሰብ ውስጥ በነበረባት የግል ችግር ምክንያት ይህንን ዘመቻ አልደገፈችውም ነበር ። ቢሆንም ብዙኀኑ ስለደገፈው ዘምታለች።

ቆንጅት ልትጠቅሰው በፈለገችውና እኔም በምስማማበት እድገት በሕብረት ወጣቱ ንቃተ ሕሊናውን ያዳበረበት ፣የህዝቡን የቀን ተቀን ኑሮ የተካፈለበት ፣ የሕዝቡን ሰቆቃ የተካፈለበት ነበር ። ብዙዎቻችንን የዴሞክራሲን መንገዱን በትክክል በጉልህ የተማርነው እድገት በሕብረት ላይ ይመስለኛል ። ስብሰባ ወግ ባለው ሥርዓት መደረግ እንዳለበት ብዙ ወጣት የተማረው እዚሁ እድገት በሕብረት ላይ ነበር ።፣ ተጨማሪ ፣ተቃውሞ ፣ ብዙኀን ፣ ውህዳን ፣ ጥያቄ ፣ ኢንፎርሜሽን ፣ ሥነ ሥርዓት፣ሞሽን፣ የብዙኀኑን ውሳኔ መቀበል እና የመሳሰሉትን በትክክለኛ የሰማናቸውና ፣ የተጠቀምንባቸው እዛው ዘመቻ ላይ ነው ። እውቀቱ የነበራቸው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በማስረዳት ከፍተኛ የሆነ ሥራ ሰርተዋል ። ይህንን በሚመለከት ቆንጅት በመጽሐፉ ላይ ትዝታችንን ትቀሰቅሰዋለች፡ -

ስብሰባው ተጀመረ ሀሳቦች ተዥጎደጎዱ ። አንዱ እጁን አውጥቶ "ሀሳብ" ይላል ፣ ሌላው ቀጥል ያደርግና "ሰፕሊመንት " በማለት ይጨምራል ፣ "ጥያቄ" የሚለው ደግሞ ይነሳል ።ይሄኛው ሲጨርስ ሌላ ይነሳና "ኦብጀክሽን " ይቀጥላል ። "ሞሽን ሙቭ ይደረግ" . . . . "ሞሽኑን ሰከንድ የምታደርጉ " . . . ወዘተ. እየተባለ ጊዜው ከነፈ ። ለእነ ፍሬሕይወት እየተደረገ ያለው አልገባቸውም ።
          ምርኮኛ ገጽ 43

በዚህ ዓይነት የስብሰባ ሥነ ስርዓት ነበር በብዙው የዘመቻ ጣቢያ ዘማቾቹ ያላቸውን ችግር በውይይት የሚፈቱት ። ቆንጅት በመጽሐፏ ይህንን ሂደት አስረድታናለች ። በዚያ ዘመን ወጣት የነበርን ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ትምህርት
አግኝተን አልፈናል ። መጭዊ ትውልድ ይህንን ዓይነቱን ስብሰባ ሳያየው ነው ያለፈው ። የደርግ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ካጠፋ በኋላ የተመሰረተው ኢሠፓም ሆነ ከዚም በታች የነበሩት መዋቅሮች በተቃውሞ የተሞሉ አልነበሩም ። ሁሉም ተጨማሪዎች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ ። ስለሆነም ተከታዩ ትውልድ ይህንን የዴሞክራሲ ጽንስ ሳያየው አልፎአል ።

በእድገት በሕብረት ወቅት የዘመቱ ወጣቶች የገበሬውንና ፣ የሠራተኛው ችግር የተረዱና መፍትሄውንም የሚፈለጉ ነበሩ። መሬት ላራሹን ለማስፈጸምም ሆነ የሠራተኛው መብት እንዲከበር ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። እንደ ዛሬው ከግል
ጥቅም አንጻር የሚተለም ፖለቲካ በዛ ወቅት ተቀባይነት አልነበረውም ። በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ዘማችና የፍሬ ሕይወት ጓደኛ አንተነህ የወቅቱ ወጣቶች ምሳሌ ነው ።

አንተነህ ስለጭቆና ሲናገር ተመስጦው በጣም ይደንቃል ። ስለመደብ አፈጣጠር ፣ ማህበረሰብ በመደብ ከተከፋፈለ በኋላ ስላለው የገዢና ተገዢ ፣ የጨቋኝና ተጨቋኝ ግንኙነት ሲያሰረዳ እርሱ ራሱ በዛ ሕይወት ውስጥ ያለፈ ነው የሚመስለው ።ሰለ ባላባታዊ ሥርዓት ፣የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ ሁኔታ ሲተነትን ብዙዎቹ ገበሬዎች በተመስጦ እስከማልቀስም ይደርሳሉ ። "መሬት ላራሹ " በማለት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ለስንት ዓመታት እንደታገሉ ሲገልጽ የደም ስሮቹ ሁሉ በስሜት ይወጠራሉ ።
          ምርኮኛ ገጽ 46

ብዙዎቻችን በኢሕአፓ ውስጥ ያለፍን ሰዎች መቼ ከኢሕአፓ ጋር እንደተገናኝን የምናስታውስው ነው ።ያ ትዝታው እስከ ሕይወታችን ፍፃሜ የምንረሳው አይደለም ።ለፍሬ ሕይወትም እንደዚሁ ። ፍሬ ሕይወት ከኢሕአፓ ጋር የተገናኘችው በአንተነህ በኩል ነው ። በፍቅርና በፖለቲካ መካካል የነበረውን ለመለየት ታግላላች ። አንተነህ ነበር ዴሞክራሲያን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታነበው ያደረገው ። እያደር ግን የሚቀጥለው እትም እስከሚወጣ ትቸኩል ጀመር ።

ፍሬ ሕይወት አንተነህ በሰጣት ትንሽ ወረቀት ላይ የተጻፈውን አነበበችው፣ እንደ ከባድ ተውኔትም ደጋገመችው ።ማምሻውን ሁሉ የሚመጣባት እሱው ነው ። ዴሞክራሲያንም በፍቅር አነበበችው ። ....

"መፋያቂያሽ ከየት ተላከልሽ" ? እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ ።ደንገጥ ብላ እጇን ከኪሷ አወጣች ።"ከጃማይካ "ብላ እጇን ከኪሷ አወጣች ።
          ምርኮኛ ገጽ 110- 111

ይህ ምን አልባት በዛ ትውልድ እንደፍሬ ሕይወት ለተጓዝን ትርጉም አለው ። ለማያውቀው ግን ምንም ማለት አይደለም ። ይህ መፋቂው የሚለው ጥያቄና ጃማይካው የሚለው መልስ የመገናኛ ኮድ ነው ። በሕዕቡ አሠራር ውስጥ የሚገናኙት ግለሰቦች ኮዱ ይሰጣቸውና አለ አስተዋዋቂ የሚገናኙበት ነው ። ይህ አሠራር ቀላል ሊመስል ይችል ይሆናል ግን ብዙ ሰው አድኗል ። በኮድ መገናኘት ሳይሆን በኮድ ስምም መጠራራት የተለመደ ነበር ። እንደዚህ ዓይነት የትግል ሥልቶችን ምርኮኛ ድንቅ በሆነ አገላለጽ ለታሪክና የሚቀጥለው ትውልድ ካሰፈለገ እንዲጠቀምበት በውስጡ አጭቆ ይዞታል።

እያደር ትግሉ እየጠነከረ ፣መስዋዕትነቱም እየተበራከተ ሄደ። በአንድ ሜይ ዴይ ሰልፍ ላይ የተከፈለው መስዋዕትነት ግን አስደንጋጭ ነበር ። 1968ሚያዚያ 23ቀን ከሰዓት በኋላ አቧሬ ላይ የተደረገው ሰልፍ እጅግ ደማቅ ነበር ።መዝሙሩ ይዘመራል ፣ መፈክሩ ይወርዳል፣ 'ባነሩ' ይውለበለባል ፣ወረቀቱ ይበተናል ።
ግድግዳዎቹ በቀይ ቀለም አሸብርቀዋል ። ....
          ምርኮኛ ገጽ 118

ለፍሬሕይወት እናቷ ቀስ በቀስ መርዶውን ሁሉ ነገሯት። ከትላንትናው ግርግር አመለጥን ብለው እየሮጡ ወደየቤታቸው የገቡትን እያነቁ በየቤታቸው በር ላይ ነበር የገደሏቸው።የሞቱት የወጣቶች ቁጥር ዘገነናት !እልህ ቁጭትና ደሟን ሲያመሩት ተሰማት ።
          ምርኮኛ ገጽ 128

ምንም መሣሪያ ያልያዙ ወጣቶች የተጨፈጨፉበት ቀን ሜይ ዴ ቀን ሚያዚያ 23 1968ዓ.ም.ምርኮኛው ላይ ሠፋ ባለ ትረካ ይገኛል ። በተለይ ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር እንዴት እንደቆሙ ፣ እንደተሰቃዩ ግልጽ አድርጎ ያሳያል ።ከአንዱ
ሁኔታ ወደ ሌላው የሚሸጋገረው ይህ መጽሐፍ በወቅቱ የነበሩት ታላላቅ ታሪክ የተሰራባቸውን ቀናት አያልፋቸውም ።

ኢሕአፓ ራሱን ይፋ ያደረገበትን ዕለት የሚረሳ ያለ አይመስለኝም ። የፓርቲው ጠላቶች እንኳ የተደነቁበት ብሎም የተጨነቁበት ጊዜ ነበር ። ዛሬ በፀረ ወያኔ ትግል ውስጥ እንደዛ ዓይነት እንቅስቃሴን የሚመኙ ብዙ ናቸው ። የሚገርመው ያንን ወጣት የጨፈጨፉት እንኳ በራሳቸው ላይ ሲደርስ የጠሉትን መናፈቃቸው ነው ።ይህ ታላቅ ወቅት ለበዓሉ የተደረገው ዝግጅት ምን ያህል እንደነበር ቆንጅት በመጽሐፋ ላይ ጠቅሳው አልፋለች ።

በሕቡዕ የሚታገለው ፓርቲ ራሱን ይፋ ለማድረግ ዝግጅቱ በየአቅጣጫው ተጧጡፏል ። አባላት ሁሉ የዚህን ዝግጅት አካል ናቸውና ከመቼውም የበለጠ ተወጣጥረዋል ። በመጨረሻ ያቺ እለት ደረሰችና የአዲስ አበባ ከተማ በፓርቲው አርማና በራሪ ወረቀቶች አሸብርቃ አደረች ። የኤሌትሪክ ገመዶች በትናንሾቹ የፓርቲው አርማዎቸ ተሞልተው የክብረበዓል ባንዲራ መሰሉ ። የቀበሌው መስተዳደርና ፖሊስ ጣቢያዎች ሳይቀሩ  በተበተኑ ወረቀቶች ተዳረሱ። የአጥሮቻቸው ግንቦችና የቤቶቹ ግድግዳዎች በቀይ ቀለም በተፃፉ መፈክሮች
አሸበረቁ ፡፡
          ምርኮኛ ገጽ 133

በዚህ መጽሐፍ ላይ የተለያዩ ሁኔታዎች ተገልጸዋል ። ስለ ሜይ ዴይ ፣ ስለ አሰሳ ፣ ስለ ድርጅታዊ አሰራር እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች በሰፊው ተገልጸዋል ። የወጣቶቹ ቆራጥነት ፣የደረሰባቸውን መከራ መቻልን በተመለከተ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ሳይጨመር ፣ሳይቀነስ ተገልጽዋል ። በተለይ ገጽ 159 ላይ ብዙዎች ሰዎች የሚያስታውሱት ታሪክ ተጽፎአል ። ሁኔታው ብዙ ትዝታ ያለበት ስለሆነ እንዳለ ቢቀርብ የሚሻል ስለመሰለኝ አቅርቤዋለሁ ።

ዘርዓይ ከወንበሩ ለጠጥ ብሎ ተንጠራራና የቀኝ እጁን ጣቶች አፍታታችው ። ከኪሱ መሀረብ አወጣና እጆቹን ፊቱን ጠራረገ። ውጭው ሙቀት ባይኖረውም የጠባቧ ክፍል የታፈነ አየር ሙቀት ፈጥሮ ፊታቸውን አወርዝቶታል ።ጋዲሳም ከቆራረጣቸው ጨርቆች በአንዱ የግንባሩን ላብ እየጠራረገ ቆም ብሎ በአቡጀዲው
ጨርቅ ላይ የፃፋቸውን ትልልቅ ፊደላት አዘቅዝቆ ተመለከታቸው ። " ኢሕአፓ ያቸንፋል " የሚለው መሐል ላይ ጉብ ብሎ ዐይን ይስባል ። ከጨርቁ መሀል ለመሀል ከፍ ብሎ ደግሞ የፓርቲው አርማ በቀይ ቀለም ደምቋል ።ማጭድና መዶሻው በሚገባቸው መልኩ ተስለዋል። ከማጭዱም ጫፍ ላይ መዋል ያለባት ኮኮብ ግን ፈንጠር ብላ የተገነጠለች መሰለው ። በርከክ አለ ኮከቧን ለማስተካከል ማርከሩን አነሳ ።

ጋዲሳ ሳያስበው ድንገት መዘመር ጀመረ ።

ለዘመናት በጭቆና ማጥ
በግፍ ሰንሰለት ታስሬ
ጨቋኙን ልጥል
ተነስቻለሁ ዛሬ
ይኼው ታጥቄአለሁ ዛሬ ...

"ጌታው ነፃ የወጣህ መሰለህ እንዴ ?"አለ አስቻለው ከሚጽፈው ላይ አንገቱን ሳያቀና
" ዳፋህ ለኛም እንዳይተርፈን ጃል" አለ ዘርዓይ ቀጠል በማድረግ። ጋዲሳም ድምጹን በጣም ዝቅ አድርጎ
መዝሙሩን ቀጠለ
. . . በአንድ እንደሚነሳ ተበዝባዡ ሁሉ
ለማያጠራጥር ድሉ
ፍፁም ነው እምነቴ
የትግሉ ነው ሕይወቴ
ልጓዝ በድል ጎዳና
በወደቁት ጓዶች ፋና

አስቻለውን ዘርዓይም ሳያስቡት አብረውት መዘመር ጀመሩ ። ወፈርና ለስለስ ያለው ድምፃቸው በዝግታ እንደሚወርድ ሙላት ውሀ ይፈሳል ፡፤

. . . የሕዝቡ ታማኝ አገልጋይ ነኝ
የሠርቶ አደሩ ወታደር
ብረት አነሳሁ
ለትግል ተነሳሁ
ጠላት ይፍራ ይሸበር
ያድር ባይ ልቡ ይሰበር
ቢሰበር አጥንቴ ቢንቆረቆር ደሜ
ላዲስ ስርዓት ልምላሜ
ፍፁም ነው እምነቴ
የትግሉ ነው ሕይወቴ ...

ግድግዳው ሦስት ጊዜ ሲመታ ሁሉም ፀጥ አሉ ። ሦስቱም ቀና ብለው ተያዩ ፣ ተግባብተዋል ። የአሰቻለው እናት ድምፃቸውን ሰምተው ማስጠንቀቂያ እየሰጡ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ የሚወስድባቸው አልነበረም ፡፤  እንደገና ወደ ሥራቸው ተመለሱ ። ዘርዓይ ስቴንስሉን ቀርፆ ሲጨርስ ማባዣውን ከአልጋው ስር አወጣ። ደስጣ ወረቀቱን ወደ አጠገቡ አቀረበ ። የማባዣውን ቀለሙን አዘጋጀ ። " አደፍርስ "ሥራውን ጀመረ ። " አደፍርስ በራሳቸው የተሠራ የማባዣ ማሽን ነው ።
ምርኮኛ 159- 160

ሰለ አደፍርስ አሰራርና ሁኔታ ለታሪክ ተጽፎ መቅረት አለበት ። የመናገር ፣የመፃፍ ፣ የመደራጀት መብት ባልነበረበት ወቅት "አደፍርስ" በዛ ወቅት የነበረውን ወጣት ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ በሕቡዕ ነፃ አውጥቶት ነበር ። ዛሬ ወያኔ
ሁሉንም የመገናኛ አውታርበዘጋበት ወቅት "አደፍርስ" የነፃነት መሣሪያችን ሊሆን ይገባል ።

ምርኮኛ ልብ እያሳቀለ የወጣቱን መከራና ስቃይ ፣የዕለት ተቀኑን ሰቆቃ የሚያስረዳ መጽሐፍ ሲሆን በውስጡ ለሚቀጥለው ትውልድ የነፃነት ትግል መሰዋትነትን እንደሚጠይቅ እያስረዳ የሚተምም ድርሰት ነው ። ቆንጀት ብርሃኑ ይህንን መጽሐፍ በመጻፏ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋ ሐውልቷን ተክላ አልፋለች ። ይህ መጽሐፍ ከዚህ በፊት ከተጻፉት ልዩ የሚደርገው የችግሩ ተካፋይና ውስጥ አዋቂ በሆነ ግለሰብ መጻፉ ነው ። በሌላ በኩል ደግሞ ገዳይና
የደርግ ባለሥልጣን የነበሩ ይህንን ታሪክ ሲፅፉትና ተገዳይና የሕዝብ ወገን የሆኑ ፣ መከታችን ሕዝብ ነው ብለው በሕዝብ መካከል የሚገኙ አመለካከቶች ምን ያህል የተለያየ እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ያሳያል ። "ምርኮኛው" የወጣቱን
ፍላጎት ፣ ዓላማና ቆራጥነት ሲያስረዳ ካለማጋነን ያለውን በንጹሕ ሁኔታ ሲያቀርበው የደርግ ደጋፊዎች የሚጽፉት ደግሞ በሕዝብ ላይ ያደረሱትን በደል ለመሸፈን ፣ትክክል ነበር ለማለት ያንን ትውልድ እንደ " አደፍርስ " ያለውን ወረቀት መባዣ የሕትመት መሣሪያ በመፍጠር የሚታገለውን አንዴ ከሲ.አይ .ኤ ቅጥረኛ ወይም የሶማሌ ሰርጎ ገብ ፣ የፔትሮ ዶላር ተገዢ እንደነበረ ለማሰረዳት ሲደክሙ ይታያሉ ።

ከአብራኩ የወጡትን ልጆች የሚያውቃቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አሁን በማይጠፋ ቀለም በታሪክ ላይ ጽፎ ከሁሉም በላይ ከፍ አድርጎ " የኢሕአፓ ጊዜ " በሚል የመሰዋትነቱንና የነጻነት ትግሉን ሲያስታውሰው ይኖራል ። ለሃገራቸው ተሰዉ ፣ለነፃነት ታገሉ ከሚለው ጎን ደግሞ "የደርግ ጊዜ " በሚል የሚታወቅ ታሪክ ይገኛል ። ይህ ታሪክ በውስጡ ወጣቶቹን ፈጁ ፣ የእርጉዝ ሆድ በሳንጃ ወጉ ፣ ታዋቂ ሰዎችን ረሸኑ ፣ ጀኔራሎቹን ፈጁ ብለውም አገራቸውን ሸጡ ፣ በመከራ ጊዜ ሸሽተው ወደ ዝምቧዌ ሄዱ ...ወዘተ የሚያካትት ነው ። ይህ " የኢሕአፓ ጊዜ " ተብሎ የተቀመጠውን ታሪክ ለማጥፋት በውሸት ላይ የተመሠረተ ተረት በመተረት የሚሞክሩ ትንሽ አይደሉም ። ዛሬ የደረግ ደጋፊዎች በሕብረተሰቡ ውስጥ ጥሩ ታሪክ ሊጽፉ የሚችሉት ጥፋትን አምኖ ንሰሀ በመግናትና የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ ብቻ ነው ።

በስተመጨረሻም ቆንጅት ብርሃኑ ከልቤ እያመሰገንኩ ። ዋጋው 45 የኢትዮጵያ ብር የሆነውን መጽሐፍ ገዝታችሁ ታነቡት ዘንድ እጠይዋለሁ ።

በልጅግ አሊ email: beljig.ali@gmail.com
 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com