‹‹የጠፈር ባይተዋሩ›› ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ<br>ክፍል ሁለት<p align='right'><font size='2'>ብርሃነ መስቀል ደጀኔ</font></p>

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

‹‹የጠፈር ባይተዋሩ›› ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ
ክፍል ሁለት

ብርሃነ መስቀል ደጀኔ

  


ገብረክርስቶስ መሳል የጀመረው ገና በሕፃንነቱ -ዕውቅ ከነበሩት ቁም ጸሐፊ ፣መጻሕፍት ደጓሽና ባህላዊ የሃይማኖት ሠዓሊ አባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ጉያ ሥር ሆኖ ነው፡፡ ባገኘው ነገር ቅርፃ ቅርፅ መሥራት ይወድ የነበረው ገብረክርስቶስ ለሥዕል ለነበረው አድልዎ - የልጅነት ቀልቡ እየገፋፋው- መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ሥዕሎች በፈጠራ ይሠራ እንደነበር ቤተሰቡም ሆነ የትምህርት ቤት ባልንጀሮቹ ዛሬ ድረስ በትዝታ ያነሱታል፡፡ ለዚህም በክብር ተቀምጣለት፣ ለጉልምስና ዘመኑ ትዝታ ከበቁለት ሥራዎቹ መሀል አንዲቱ የሰባት ዓመት ሥዕሉ ‹‹ምስለ ፍቁር ወልዳ›› ምስክር ናት፡፡ 

ከሌላ በኩል፣ አብረውት ከተማሩት መሀል፣ ሐረር ተወልደው ያደጉትና ዛሬ በኢትዮጵያ የአማርኛ ዘመናዊ ግጥም ስልት -ልዩ የአሰነኛኘት ዘዬ ያላቸው አቶ ሰይፉ መታፈሪያ አንዱ ናቸው፡፡ ገብረክርስቶስ ደስታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ከሐረር አዲስ አበባ እስከሄደ ድረስ፣ ስለሱ የሚያስታውሱት አላቸው፡፡ 

ገብረክርስቶስ! ያኔ በክፍል ደረጃ ይበልጠኝ ነበር፡፡ በጣም የሚሮጥ ቀልጣፋና ሳይደክም የሚጫወት ነበር፡፡ ቴኒስም እንጫወት ነበር፡፡ አቋሙ ሁሉ የስፖርተኛ ነበር፡፡ . . . ሌላ ትዝ የሚለኝ! ያኔ በባዶ እግር ነበርን፡፡ ምንለብሰውም ቁምጣ ነበር፡፡ ታዲያ ማስታወስው ጧት ወይ በእረፍት ሰዓት ቁጭ ብለን ፀሐይ ስንሞቅ፣ ቁጭ ብሎ ጉልበቱ ላይ ይሥል የነበረው ነው፡፡ በሚሥላቸው እደነቅ ነበር፡፡ ያለምንም ጥርጥር የስን-ክን ሰው ነበር፡፡ በስን-ክን ስሜት የተነደፈ ልጅ ነበር፡፡ . . . ዛሬ ግን የሚያሳዝነው አፅሙን እንኳ ለሀገሩ መሬት ማብቃት አለመቻላችን ነው፡፡ 

ገብረክርስቶስ ደስታ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ የመጣው በ1939 ነው፡፡ በያኔ የኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት /የዛሬው መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ/ ተመደበ፡፡ ከሐረሩ የጢቆ አደሬ መካነ ሥላሴ ደብር አለቃ ከነበሩት ከአለቃ ለማ ኃይሉ ልጅ- ከመንግሥቱ ለማ ጋር በወግ ለመተዋወቅ የቻሉትም እዚሁ ነበር፡፡ ገብሬ ፣ትምህርቱን በአዳሪነት ጀመረ፡፡ 

ከዚሁ ከኮተቤ ቆይታው ሊዘከር የሚችል ነገር ቢኖር አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ መምህሩ ጋር ተጋጭቶ ከትምህርት ቤት መታገዱ ነው፡፡ እግዱም በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ነዋሪ የነበረው የዚህ መምህሩ ውሻ ሊነክሰው ሲጋበዝ ውሻውን በመደብደቡ ነበር፡፡ መምህሩ ለውሻው መመታት ተቆርቁሮ - ዳይሬክተሩ ላይ ይከሰዋል፡፡ ዳይሬክተሩም አስጠርቶት ‹‹ይቅርታ ጠይቅ! ››ይለዋል፡፡ ‹‹እኔ ይቅርታ ልጠየቅ ሲገባ፣ ይህ አግባብ አይደለም›› ይላል፡፡ ለሱ መታዘኑ ቀርቶ! ‹ለፈረንጅ ውሻ› ሲዳላ በማስተዋሉ፣ በደመ-መራራነት ተናገረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከበላዮቹ ጋር በመሟገቱ እንደ ‹ድፍረት› ተቆጥሮበት እንዲያውም እስከመታሠር አደረሰው፡፡ ለግሳፄ ተብሎ በያኔው የሦስተኛ ሻለቃ ክቡር ዘበኛ ካምፕ ለአራት ወራት ያህል ታሠረ፡፡ 

ያኔ በልጅነቱ-በጣሊያን ወረራ -የ‹‹ባዕድ ሀገር›› ጥቃትን ያየው ገብረክርስቶስ፣ ‹‹የፈረንጅ ዕውቀቱን እንጂ ክፋቱን የማይፈልገው›› ገብሬ፣ በበሰለ መንፈስ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹የባዕድ ሰው›› ጥቃትን እስከ እስር ድረስ ተጋፈጠ፡፡ በዚህ ሁኔታ ትምህርቱን ለማቋረጥ ቢገደድም፣ ይህ ጊዜ እንደዝንባሌው የመሣል፣ አንድም በጥበቡ ዘርፍ ጭምር በስፋትና በጥልቀት በማንበብ መልካም አጋጣሚን ያተረፈለት ነበር፡፡ ከአእምሮው ብልጽግና ሌላ፣ ገብረክርስቶስ ከእግር ኳስ ችሎታው በተጨማሪ አካሉን ለማዳበር የአካል ማሠልጠኛ ጂምናስቲክ ማዘውተርና ሰውነቱን በስፖርት መገንባት የጀመረው ይኼኔ ነበር፡፡ 

ያቋረጠውን ትምህርት፣ በለጣቂው ዓመት የጀመረው፣ ያኔ ጉለሌ አዲስ በተከፈተው የጄኔራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ዊንጌት መግባቱ፣ ከቀለም ትምህርቱ ጎን ስለጥንታዊውና ዘመናዊው የአውሮፓ ሥነ-ጽሑፍና ሥነ ጥበብ በሰፊው ለማንበብ ሌላ ልዩ አጋጣሚን ፈጥሮለታል፡፡ የገብረክርስቶስ ወርቃማ የወጣትነት ወቅት፣ ይህ ዊንጌት ያሳለፈው የሦስት ዓመታት ጊዜ ነበር፡፡ የቀለም ትምህርቱ፣ የግል ንበባቡ፣ ስፖርቱ ወዘተ፡፡ በቀለም ትምህርት ትጋቱም ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ተሸላሚ ለመሆን ችሏል፡፡ አድናቂውና የጥበብ ባልንጀራው ከነበረው ከሰሎሞን ደሬሣም ጋር የተዋወቀው በዚሁ በዊንጌት የተማሪነት ወቅት ነበር፡፡ 

ከዊንጌት ደማቅ ትዝታዎቹም የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ገብረክርስቶስ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለ፣ የትምህርት ቤቱ ዓመታዊ በዓል ሲከበር፣ የተማሪዎች የሥዕል ኤግዚቢሽን ቀርቦ ነበር፡፡ በበዓሉም ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተገኝተው ነበር፡፡ ታዲያ ያኔ  በኤግዚቢሽኑ -ለሀገሪቱ የሥዕል ባህል አዳዲስና እንግዳ የሆኑ የአሣሣል ስልቶችን ይዞ የቀረበው ገብረክርስቶስ ነበር፡፡ የልጅነት ማደጎውንም የምታስታውሰው ‹‹የሐረር ገበያ›› ሥዕሉንም ያቀረበው በዚህ ኤግዚብሽኑ ነው፡፡ እና ‹‹ሪአሊስቲክ›› ‹‹ሰሚ አብስትራክት›› እና ‹‹ አብስትራክት›› /ረቂቅ ወይም ምስጢራዊ/ የሆኑ ዘመናዊ ሥዕሎች ነበሩ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ታዲያ ንጉሡ በአድናቆት ጭምር አነጋግረውት ነበር ይባላል፡፡ እኒያን ‹‹አብስትራክት›› ሥዕሎቹን እያዩለትም ‹‹. . .መቼም ነገሩን አጥተኸው ሳይሆን - ሆነ ብለህ ለማበላሸት ብለህ ነው እንዳሉት ››ይነገራል-ፈገግታ በተቀላቀለው አንደበት፡፡ 

ገብረክርስቶስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከዊንጌት በ1942 አጠናቀቀ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳለ ነበረ በለጣቂው ዓመት በ1943 ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተከፈተው፡፡ የኮሌጅ ትምህርት ለመቀጠል ከገቡት ከመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መሀል አንዱ ገብሬ ነበር፡፡ ፍላጎቱ ሥነጥበብ ለማጥናት ነበረ፡፡ ይሁንና ሀገሪቱ ይህን ፍላጎቱን ልታሟላለት አልቻለችም፡፡ የገሀሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና በመሆኑ ፣ከዚሁ የሀገሪቱ የወደፊት ግስጋሴና ዘመናዊ ዕድገት አንፃር ራሱንና ሀገሩን ለመርዳት፣ ገብሬ እርሻ ማጥናት እንዳለበት ወሰነ፡፡ በሳይንስ ፋካልቲ የሥነ-ሕይወት / ባዮሎጂ/ ዲፓርትመንት ተማሪ ሆኖ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ይህ የኮሌጅ የመጀመሪያ ዓመት ለገብረክርስቶስ መልካሙ ጊዜ ነበር፡፡ በአዲስ የትምህርት ሥርዓት፣ በአዲስ ፍላጎት ከመማር ሌላ፣ በስፖርቱም በኩል ለፋኩልቲው የእግር ኳስ ቡድን ምርጥ ተጫዋች ነበር፡፡ ሆኖም ሁለተኛ ዓመት ካጋመሰ በኋላ፣ የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ ወጣ፡፡ 

ከኮሌጅ ሕይወት ‹‹ስደቱ›› በኋላ፣ ለጣቂዎቹ አምስት ዓመታት /1944-1948/ ለገብረክርስቶስ አታካችና መራራ ወቅቶች ነበሩ፡፡ ገብረክርስቶስ ‹ራሱን ፍለጋ› ያልገባ ያልወጣበት ያልወረደውና ያልጣረው ነገር አልነበረም፡፡

 ኮሌጁን አቋርጦ መጀመሪያ ሥራ የያዘው በአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ነበር፡፡ የአፈር ምርመራ ባለሙያ ሆኖ በዚህ ድርጅት ጥቂት ጊዜያት ሠራ፡፡ በሥራው የመንፈስ እርካታ ባለማግኘቱ ጥሎት ወጣ ::በመሆኑም ትንሽ ጊዜ እቤት ማሳለፍ ተገደደ፡፡ ቆይቶ ግን - ተወልዶ ባደገበት ሐረር ሥራ አገኘ፡፡ ሲንክላር የተሰኘው የአሜሪካ ነዳጅ ፈላጊ ድርጅት ቀጥሮት ኦጋዴን ወረደ፡፡ በጤና ምክንያት ዓመት እንኳ ሳይቆይ ሥራውን ጥሎ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ አሁንም ትንሽ ጊዜ ቤት ማሳለፍ ግድ ሆኖበት ነበር፡፡ በሥዕል ዝንባሌው ምሉዕ መግለጫ ጊዜ ያገኘበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ 

ቆይቶ ግን በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ ተቋማት ከሚባሉት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደስታስቲሺያን የሠራ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ለተወሰነ ጊዜ ሠርቷል፡፡ ዛሬ በባንክ ባለሙያዎች ክበብ እና በሞርጌጅ ባንክ የሚገኙ ሥዕሎቹ ከዚሁ ቆይታው ጋር የሚዛመዱ መታሰቢያዎቹ ሳይሆኑ አልቀረም፡፡ ይሁንና እዚያም ብዙ አልቆየም፡፡ ይሻላል በሚል እምነት፣ በስብስቴ ነጋሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጠረ፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ጂኦግራፊ እና ጠቅላላ ሳይንስ አስተማረ፡፡ በዚህም አልገፋበትም፡፡ 

በመጨረሻ ‹‹ራሱን ፍለጋ›› ላይ የነበረው ገብረክርስቶስ ‹‹ሥራ›› የሚባል ነገር እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ቤቱ ሆኖ-በሥዕል ሥራው ላይ ብቻ በመጠመድ ያለዕረፍት መሥራት ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ  ነበር- በሕይወቱም በዝንባሌውም የመጀመሪያ እርካታ ያገኘበትን ፍሬ የቀመሰው፡፡ በ1946 በኢትዮጵያ የሥነጥበብ መድረክ፣ እንደ ጥበብ ወፍ ብቅ አለ፡፡ በወቅቱ የአሜሪካ የማስታወቂያ ድርጅት አካል በነበረው ቤተ መጻሕፍት ዘመናዊ የአሣሣል ስልቶቹን ያስተዋወቁ እና የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የዳሰሱ የ‹‹ድሆች ቤተሰብ›› ምዕመናን ›› ወዘተ. የተሰኙ ስዕሎቹን ትርኢት አሳየ፡፡

 በጀርመን ከሄደ በኋላ በቦን፣ ከተለያዩ የጀርመን፣ የፈረንሳይ እና የሩሲያ አርቲስቶቸ ጋር በቡድን ሆኖ በጀርመን የሥነጥበብ አፍቃሪዎች ዘንድ ዝና ያተረፈለትን የሥዕል ትርኢቱን በቤትሆቨን የአርት አዳራሽ ለማሳየት በቃ፡፡ ለልዩ ተሰጥኦው የጀርመን መንግሥት የአንድ ዓመት ነፃ የመኖሪያ ፍቃድና ስቱዲዮ ስለሰጠው ገብረክርስቶስ የአውሮፓን ዘመናዊ የጥበብ መንፈስ እና የአሠራር ስልት እያጠና ለተጨማሪ አንድ ዓመት ቆየ፡፡ በወቅቱ በአውሮፓ የ‹‹ኤክስፕሪሽኒዝም›› የሥነ ጥበብ ፈለግ ተከታይ አርቲሰቶች ጋርም አብሮ የመሥራት አጋጣሚን አደለው፡፡

 በዚሁ የጀርመን ቆይታው ከሚያፈቅራት ሀገሩ፣ ከሚወደው ቤተሰቡና ትዝ ከምትለው የትውልድ መንደሩ ርቆ በ‹ባዕድ ሀገር ››የናፍቆት ደም ያረገዘ ብዕሩን መስበቁ አልቀረም፡፡ ‹‹‹ሀገሬ ››እና ‹‹እንደገና›› የተሰኙ ፍቁረ ኢትዮጵያ ውብ ቅኔዎቹ የተማጡት ያኔ ነበር፡፡

 ምናልባትም ናፍቆቱን እና አንዳንድ የመንፈስ ችግሩን በጋራ ይካፈሉት ከነበሩት እና በጀርመን ሀገር በተለያዩ ከተሞች ይማሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከነዕጓለ ገብረ ዮሐንስ /ዶ/ር/፣ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ /ዶ.ር/፣ አምሳሉ አክሊሉ /ዶ.ር/፣ አሉላ አባተ /ዶ.ር/፣ ኃይለገብርኤል ዳኜ /ዶ.ር/፣ ወዘተ  ጋር መተዋወቅ የቻለው በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ 

ገብረክርስቶስ ካንድ ዓመት ልፋት፣ ጥረትና ድካሙ ጋር ባጠቃላይ ጀርመን ሳለ 90 ያህል ድንቅ የተባሉ ሥዕሎቹን ሳለ፡፡ ስብእናን የሚገልጸውን ‹‹እኔ በገዛ እጄ›› የተሰኘ የገዛ ገፀ ምስሉን የሣለው በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ ባህላዊውን የሀገራችንን እና ዘመናዊውን የአውሮፓ ጥበብ እና የሥልጣኔ መንፈስ በገዛ መንፈሱ የዕውቀትና የጥበብ ድልድይነት አዋህዶ በዘመናዊነት ኢትዮጵያ ሀዲስ የጥበባት ዘር ሊዘራ፣ ሞገደኛ የጥበብ ተምኔቱን የፀነሰው ይኼኔ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የገናና ስብእናው ዘመናዊና ህብራዊ ትርኢቶች በውል መገለጽ የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 

ታዲያ የጀርመን ቆይታ ሥዕሎቹ በጀርመን ሃያስያን እንደተገለጹት የአርቲስቱን ዘመናዊ ጠቢብነት የሚያውጁለት፣ የጀርመንን መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንድም የአካላዊ ሥልጣኔዋን ማቴሪያላዊ የኢንዱስትሪ ውጤት ቁሳቁስ እንዲሁም መልክአ ሰብእ የሚገልፁ ብሎም ከገዛ ሀገሩ ሕይወት እና ትዝታ ከገዛ ስብእናው ጭምር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አሣሣል ቴክኒካቸውም ግማሽ ምሥጢራዊነትን እና ምሥጢራዊነትን /ሰሚ አብስትራክትና አብስትራክት/ እንዲሁም እውነታን /ሪአሊስቲክ/ የሚያንፀባርቁ ነበሩ፡፡ እነዚህን ጠቅላላ ሥራዎቹን በዚሁ በ1954 ኮሎኝ ከተማ በሚገኘው በኩፐርስ ጋለሪ አዳራሽ፣ የያኔው የኢትዮጵያዊ አምባሳደር /ሜ.ጀኔራል ከበደ ገብሬ/ በተገኙበት ለጀርመን አፍቃሬ ጥበባት አሳየ፡፡ ትርኢቱ አድናቆት ከማትረፉም በላይ፣ ገብረክርስቶስን በጀርመን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና የመጀመሪያው ድንቅ አፍሪካዊ ሠዓሊ የሚል ማዕረግ አስገኝቶለታል፡፡ ይኸው ክብር እና ዝና ከጀርመን ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ዘንድ ሞገስ አስገኝቶለት በስታድትሆል አዳራሽና በጉድስበርግ የ90 ሥዕሎቹን ትርኢት የማሳየት ተጨማሪ ክብር አገኘ፡፡ 

ገብረክርስቶስ ወደ ሀገሩ ከመመለሱ በፊት አውሮፓን እንደጠቢብም እንደ ‹‹ቱሪስት››ም ዞረ፡፡ ጥንታዊቱን የፍልስፍና እና የጥበብ አምባ ግሪክን፣ ቤልጅግን፣ ፈረንሳይን፣ ስፔንን እና ጣሊያንን ጎብኝቶ እና የሥዕል ኤግዚቢሽኖቹን አሳይቶ በመጋቢት ወር 1954 ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ 

የሀገሩን ወጣቶች የሥዕል ጥበብ ለማስተማር ብርቱ ተምኔት እንዳለው የገለጸው ገብረክርስቶስ በ1955 ያኔ በትምህርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር ሥር ይገኝ በነበረው በአዲስ አበባው ብቸኛ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሥራውን ጀመረ፡፡ ራሱን በማስተማር ሙያ ላይ አሰማርቶ፣ ሙሉ ጊዜውንም ለጥበብ ሰጥቶ ያለዕረፍትና ድካም በመሥራት ከጀርመን ሀገር በተመለሰ በዓመቱ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተገኙበት በአ.አ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ግንቦት 3 ቀን 1955 ዓ.ም የ72 ሥዕሎቹን ኤግዚቢሽን አሳየ፡፡ 

እኒሁ ሥዕሎቹ ባመዛኙ በወቅቱ ጀርመን ውስጥ በዘመናዊ ጥበብ ስልት ረገድ ገናና የነበረውን ‹‹ኤክስፕሬሽኒዝም›› የተሰኘውን የሣሣል አቅጣጫ የተከተሉ፣ በይዘታቸውም የመልክአምድር፣ የቁሳቁስና የመልክአ ሰብእና የያዙ ድርሰቶች ሲሆኑ በቴክኒካቸውም የውሃ ቀለም፣ የዘይት ቀለም ቅብ እና የግራፊክስ ሕትመት ሥራዎች ነበሩ፡፡ እኒሁ ሥራዎቹ የጠቢቡን ልዩ ክሂሎትና አዲስ የሥነጥበብ አቅጣጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ያበሰሩ እና የተለሙ ነበሩ፡፡ 

ሁነቱ አድናቆትና ተጋጭ የሆኑ አስተያየቶችን አስከትሎበታል፡፡ ከልማዳዊው ሥዕል ስልት ፍፁም አፈንግጠው ለቀረቡት ሥዕሎቹ ለ‹‹ሀገሪቱ ባዕድ ናቸው ››የ‹‹ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናዊ አርት አይገባውም ›› ‹‹ጊዜውን የተከተሉ አይደሉም ›› የሚሉ የወቀሳ አስተያየቶች ጎርፈው ነበር፡፡ እውቁ የበረከተ መርገም›› ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ/ገሞራው/ እንኳ ‹‹መዳልወ ኪነት››  በሚለው ግጥሙ የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል ‹‹እውነት አብስትራክት አይደለችም ››በሚል ብሂል፡፡ 

ገብሬ ለእኒህ ‹‹ወቀሳዎች ››በእርጋታና በአስተውሎት ሊመልስ ሞክሯል፡፡ ይህም ግንቦት 5 ቀን 1955 ታትሞ በወጣው የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ላይ በወግ ተዘግቦ እናገኘዋለን፡፡ 
‹… የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ /1946/ ለመጀመሪያ ጊዜ ላሳዩት የአብስትራክት አርት ሥዕሎቼ ብዙ ደጋፊዎች አግኝቼ እንደነበር አስታውሳሁ፡፡. . ./የአሁኖቹ/ ሥዕሎቼ በአዲስ አቅድ የተዘጋጁ ቢሆኑም፣ ለሀገራቸው ሕዝቦች /ለአውሮፓውያን/ እንግዳ ጥበቦች አይደሉም፡፡ . . . የኢትዮጵያም ሕዝብ ይህን በመሰለው የፈጠራ አሠራር፣ ያላያቸው ልዩ ልዩ መልክ ይዘው በጣና ባሕር ባሉት አብያተ ክርስቲያናትና በደብረ ዳሞ እንዲሁም በላሊበላ ሕንፃዎች በቅርፅ ተሰርተው ይገኛሉ፡፡› 
ሲል ገልፆአል፡፡ ገትጋታ ባህለኞችም በአሽሙርና በማካኪያስ አላዋቂነታቸውን ደጋግመው ሲያስተጋቡም በወቅቱ በእርጋታና በአስተውሎት ሳይሰለች ምላሽ ሊሰጥ ሞክሯል፡፡ 

‹‹… እኛ በመልማት ላይ በሚገኙት ሀገሮቻችን ዘመናዊ ሕንፃዎችን፣ ዘመናዊ አውቶሞቢሎችን፣ እናሽከረክራለን፡፡ በጠቅላላ በቴክኖሎጂ፣፣ በሳይንስ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ኢንተርናሽናል / ዓለማቀፋዊ/ ሥራዎችን እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ኪነጥበብ ብቻ ለምን ይለያል?... ሁሉም የነበረውንና ያለውን ጠብቆ ለማቆየት ብቻ መሰለፍ የለበትም፡፡ እንደሌላው ዘርፍ ሁሉ ለኪነጥበብም መሥራትና አስተዋዋቂም ይፈልጋል፡፡…..››

 አለ ገብረክርስቶስ፡፡ ባጠቃላይ አዲሱንና ዘመናዊውን የጥበብ መንፈስ ከአውሮፓይቱ ጀርመን ተክኖ እና በ‹‹ፋውስታዊ ››ተምኔት የመጣው ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ለሁለቱ የኢትዮጵያ /ባሕላዊ/ እና የአውሮፓ /ዘመናዊ/ ሥልጣኔ ጥበባት አማካይ ጠቢብ ሆኖ በገዛ ወዙ የተጥለቀለቀ አዲስ የመንፈስ ሕይወት ራዕዩን በቀለምና በቡሩሹ ኃይልና ውበት አዲስ ዓለም ለዚህ ኢትዮጵያ ትውልድ ገለጠ፡፡ እና ‹‹ረቂቅ›› ‹‹ሥውር›› ‹‹ምስጢራዊ›› ‹‹ግልጽ ያልሆኑ›› ‹‹አብስትራክት›› ወዘተ. የሚል ‹‹ክርስትና ስም›› ያተረፉቱ ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ የሥዕልና የሥነጥበብ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ሀዲስ ምዕራፍ ከፈቱ፡፡ ‹‹መልስ ወዳገር ቤት፣›› ፣‹‹የካቲት 12››፣ ‹‹ያለፈው መልካሙ ጊዜ››፣‹‹የሐረር ገበያ››፣ ‹‹እኔ ነኝ››፣ ‹እኔ በገዛ እጄ›፣ ‹‹ጎልጎታ›› ‹‹ጂፕሲ ልጃገረድ››፣ ‹‹ቀይብርሃን››፣ ‹‹የድሆች ቤተሰብ››፣ ‹‹በራሪ ወፍ››፣ ‹‹በቁኤት››፣ ‹‹ ጠላቂ ጀምበር››፣ ‹‹ፀደይ›› ዘተ. የተሰኙት ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል ታሪክ አንዳች የሀዲስ ፍኖት ፋና ወጊ ሆነው ሀዲስ የሥነጥበብ ምዕራፍ ገብረክርስቶስ መክፈቱን በእርግጠኝነት አውጀውለታል፡፡ 

ገብረክርስቶስ ደስታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ የጥበብ ሐተታ አይደለም ፡፡ ባጭሩ፣ ነቢይ በ‹‹ሀገሩ አይከበርም›› እንዲሉ ወይም ‹‹ትንቢት ይቀድሞ ለነገር ››እንዲሉ የሕይወት ትራዤዲው ትንቢት ነው መሰል ከሀገር ተሰዶ ከመውጣቱ ትንሽ ቀደም ብሎ በ1969 በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከልጅነት እስከ ጉልምስና ድረስ ያፈራቸው የምርጥ ሥዕሎቹን ኤግዚቢሽን ‹‹አጠቃላይ የሥዕል ትርኢት›› በሚል ለመጨረሻ  ጊዜ አሳይቶ ለመጨረሻው አልፏል፡፡ 

መጋቢት 21 ቀን 1973 በ‹‹ባዕድ ሀገር›› በሞት የተለየን እና የዚህ ትውልድ ‹‹የከርታታ ነፍስ ምሳሌ›› የሆነው ገብረክርስቶስ ያ ታላቅ ኢትዮጵያዊ እና ዓለም አቀፋዊ አርቲስት ከተለየን እነሆ ሃያ ዓመታት ሊመጡ ነው፡፡ 

ይሁንና ዛሬ በጥበብ ሥራዎቹ መታሰቢያነት መሀላችን ሕያው ነው፡፡ ይህንኑ ተአምኖዬን የሚያፀድቅልኝና በእያንዳንዱ አፍቃሬ ጥበብ ዘንድ ዛሬም ሕያው መሆኑን የሚመሰክር ማራኪ ዝክር ሳልጠቅስ ማለፍ አይሆንልኝም፡፡ በቅርቡ፣ የገብረክርስቶስ ዘመነኛ እውቁ ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም በቅርቡ ባወጡት ‹‹ሹክታ›› በተሰኘ የትውስታ መድብል /1992/ ውስጥ  ገብረክርስቶስን እና መሰል ጠቢባንን ‹‹የእግዜር ባውዛ›› ሲሉ ሰይመዋል፡፡ ለዚህ ትውልድ ገብረክርስቶስ ከዚህ በላይ ምን ድንቅ ዝክር ይኖራል?!! 



ሪፖርተር መጽሔት፤ጥቅምት 1993 ዓ.ም
 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethioreaders.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
mengesha tesfaw [1754 days ago.]
 pleace i want read abey mengstu lema (Ygtsm gubae)

አበራ [1421 days ago.]
 ስለ ገብረክርስቶስ ይቺን አግኝቼ ላክሁላችሁ። http://lissanonline.com/blog/?p=584 አበራ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com