Warning: Undefined array key "access" in /home2/negadras/public_html/ethioreaders/articles/index.php on line 1
 <font size=5>ኢሕአፓ ፣ እኔ እማውቀው </font> <br> ከሰላሙ ባላይ

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

ኢሕአፓ ፣ እኔ እማውቀው
ከሰላሙ ባላይ

  


ከሐገር ውስጥ የተላከልኝን የሕይወትን ተፈራን መጽሀፍ፣ አገላብጬ አየሁትና ደሞ ይቺ ማናት? ምን ልትል ነው? ጌታቸው ማሩ? አልኩና መልሼ አስቀመጥኩት። ይሄ በሆነ በሶስተኛው ቀን  እንደኔው የእዚያ ትውልድ ዓባል የሆነች የማውቃት ሰው ደውላ፣ ስለዚህ መጽሀፍ የሚወራውን ነገረችኝ። አሁንም እያቅማማሁ፣ አንድ ሁለት ገጽ እያልኩ ሞከርክቱ። ከገባሁበት በኋላ ግን ላቆመው ቸገረኝ፤ ምክንያቱም  ሕይወት ተፈራ መጽሀፉን የጻፈችው ስለ ኢሕአፓ ሳይሆን ስለ እሷ ኢሕአፓነት በመሆኑ የእኔንም ኢሕአፓነት እነደገና ገነፈለና ወደ እዚያ ዘመን መለሰኝ። 

የሕይወት ተፈራ  መጽሀፍ ለማንበብ ይመቻል። አጻጻፏ እራሷን ባለ ታሪክ አድርጋ ስላቀረብችው ቀላል አድርገዋለች።  ከላይም እንዳነሳሁት የጻፈችው ስለ ኢሕአፓ አይደለም ስለ እሷ የኢሕአፓነት ታሪክ ነው። ከመጽሀፉ ድምጸት የኢሕአፓነት ታሪኳን እውነቱን እንደጻፈች ነው የተሰማኝ። በዚህ አኳያ ለሌሎችም መልካም ምሳሌ ሆናልችና ላመስግናትም እወዳለሁ።

የሰራሁት ስሌት ትክክል ከሆነ፣ በእድሜ ከሕይወት በጥቂት አመታት የማንስ ይመስለኛል፤ በኢሕአፓነቴ ግን በመጽሀፏ ላይ የተጠቀሰቻቸውን ጓዶች ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹን አውቃቸዋለሁ። በርካቶቹ በትግሉ ተስውተዋል። እኔም እንደ ሕይወት ተፈራ ታሪክ ብዙ አጋጣሚዎች  አሲረው በህይወት እንድተርፍ አድርገውኛል። እሷም በምትለው የእሥር ዘመን በከርቸሌ  ለአምስት አመት ያህል ታስሬ ነበር። ሕይወት በድርጅት ስራ ታገኛቸው ከነበሩት ወድማማቾች ሲራክና ቲቶ በተጨማሪ ፍቅሩ የሚባል ሌላ ወንድም ነበራቸው። ከከርቼሌ ውስጥ ተወስዶ ነው የተገደለው ። እኔም የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ነበር  የታሰረው። እስከማስታውሰው ድረስ የተያዘው ቀለል ባለ ጉዳይ ነበር ። በኋላ ግን እዚያው እያለ  ከውጭ በመጣ ችግር ነበር ለመገደል  የበቃው።

በመጻህፏ ውስጥ እንዳየሁት እሷ በህይወት በመትረፏ ምስጋና አቅርባለች። እኔም በሕይወት መትረፌን ያኔም ይሁን አሁን ሳልፈልገው ቀርቼ አይደልም፣ እንደ ሕይወት ግን ለመስጋና የሚያደርስ ምክንያት እንዳለኝ እርግጠኛ አይደለሁም። እሷም  እንዳለችው ምንም ዓይነት በዓለም ቅራቅንቦ የሚቀሰቀስ ስሜት የለኝምእድሜ ለኢሕአፓ ። ከእዚያ ውጭ ሀይማኖተኛ  አይደለሁም ። ኢሕአፓነቴ የሚጀምረው በዚህ ነው፣ በዚህ ረገድ ዛሬም ኢሕአፓ ነኝ። አንዳንድ  ጊዜ ሳስበው ጓዶቻችን በሙሉ ለንሰሐ ጊዜ ሳያገኙ ነው የተሰውት። ዛሬ ተለይቻቸው ንሰሀ ብገባ፣ አብሬአቸው የገባሁትን ቃል ኪዳን ያፈረስኩ ይመስለኛል።  አሁን ያለው ማንነቴ የተቀረጸው በኢሕአፓነቴ  ነው።

እንደማናቸውም ጓዶቼ ኢሕአፓ የሆንኩት እነ ጌታቸው ማሩ በሚመሩት አብዮት ቡድን በኩል ነው። ለእኔ ምናልባትም እስከማስታውሰው ድረስ በጊዜው አብረውኝ ለነበሩት ጓዶቼ ኢሕአፓ ሁሉም ነገር ነበር። የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ። በጊዜው እናቴም አባቴም የመንግስት ሰራተኞች በመሆናቸው ቤት ውስጥ ችግር የሚባል ብዙ አይታወቅም። ኑሮውም  እንደዛሬው  ከባድ   አልነበረም። ድህነትና   ጭቆና ህዝቡን እንደ የዛሬው የውርደት ደረጃ  አላደረሰውም ነበር። ቤተሰቦቻችን በሰጡን አጋጣሚ ዘመናዊ ትምህርት ተምረን የራሳችንን ሕይወት የምናቸንፍበት እድል ነበር። በተፈሪ መኮንን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነው፣ መጀመሪያ ከአብዮት ቡድን ጋር የተገናኘሁት፣ በኋላ ደግሞ ወደ ኢሕአፓ የገባሁት።

በሌላው መልኩ የአደግንበት ማህበረሰብ በጣም ጨካኝ BRUTAL ነበር። እንደ ልጅ በኋላም እንደ ወጣት ምንም ዓይነት ቦታ አልነበረንም። ሁሉም ጉዳይ የሚቋጨው ጉልበትን መሰረት ባደረገ ስሌት ነበር። ቤተሰብ ልጆቹን ያለምንም ገደብ የፈለገውን የማድረግ መብት አለው።ማናልባት ይሄ መግደለን ላይጨምር ይችላል ታላላቆች  በታናናሾች ላይ መብት አላቸው። እግራችን ከቤት ሲወጣ የመንደሩ  ዓይን አስፈሪ ነው። ማንም ወላጅ የሌላውን ልጅ በተለይ ሥርዓት በማስያዝ ሰበብ አድርጎ ከሆነ፣ መምታት መብቱ ነው። የሰፈር ጎረምሳ ደግሞ አለ። ና ኪስህ ውስጥ ምን ይዘሀል? የሚል። ት/ቤት ያሉ አስተማሪዎች ለትምህርት ከሚያጠፉት ጊዜ ይልቅ ተማሪ በመደብደብ የሚያጠፉት ጊዜ ይበልጣል። ከዚህ አለፍ ሲል መንግስት የሚባል ነገር አለ፣ በጣም የሚፈራ ። ቄሱ ያስፈራሉ።  እግዚአቢሄር ይፈራል። ንጉሱ በእግዛብሄር የተቀቡ ናቸው፣ ያስፈራሉ። ይሄ ብቻ አይደለም የሰፈሩ ውሻ ያስፈራል፣ ምክንያቱም ይናከሳል፣ፈንጆች ውሻ ሲስሙ እያዬሁ አሁንም ድረስ ይገርመኛል ፣  አህያዋን እንኳን መጠጋት አይቻልም፣ ትራገጣለች። ላሟም ትዋጋለች። በዚህ ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ እያለን ነው፣ ኢሕአፓ የመጣው።

ሕይወት ተፈራ  በመጽሀፋ ውስጥ የአንድ በድብቅ የሚሰራ ድርጅት አካል መሆኗ የተነገራት ዕለት የተሰማትን ፍንደቃ ስሜት ነው፣ እኔንም የተሰማኝ ። በቅርብ የምንተዋወቅ ጓደኛሞች እየተሰባሰብን ማርክሲዝምን ማጣናት ከጀመርን  ከረም ብለን ነበር ። አንድ ቀን ተሰብሰበን እንዳለ ከመሃከላችን ከባላይ አካል ጋር የሚያገናኝ መስርመር ኖሯል መሰለኝ፣  አንዱ ጓዳችን፣  የስውር  ድርጅት ዓባል መሆናችንን ነገረን። የእዛን እለት መጋረጃው ተቀደደ።  የተለይ   ስሜት ተሰማን። እርስ በእርሳችን የምንተያይበት አይን ተለወጠ።  ጓደኛነታችን ፈረሰ ፣ ጓዶች ሆን። ያን እለት ወደ ቤቴ ስመለስ አረማመዴ ተቀየረ። ትልቅ ነገር ከትከሻዬ ወረደ።

እየቆየ  የመንደሩ ውሻ ማስፈራቱን አቆመ፣ ላሟ አትዋጋም፣ ቤተሰብ አያስፈራም፣ የመንደር ጎረምሳ ዋጋ የለውም፣ መንግስት  ገደል ይግባ፣ ንጉሱ ዘሬ ይውረዱ፣ ምክንያቱም እግዚአብሄር የለማ። ይሄን ማን ያለው? ኢሕአፓ ፣ እሱ ማነው? ማን ያውቃል፣ ለምንስ ይጠየቃል። በአጭር አነጋገር ነጻ ወጣን። ለመጀመሪያ ጊዜ በማሕበረሰቡ ውስጥ እንደሰው ተቆጠርን። እንደውም  ከረመና እንፈራም ጀመር። ለእኛ ኢሕአፓ ሁሉኑም ነገር የሆነው ለእዚህ ነው።

የኢሕአፓ ፍቅራችን የሚመጣው ማንነታችን ከማረጋገጥ EXISTENTIAL ምክንያት  እንጂ፣ ደርግ ፋሽስት ነው ወይስ ቦናፓርት፣  የከተማ ትጥቅ ትግል ትክክል  ወይስ አይደለም፣ ከሚሉ  ትንተናዎች ተነስተን አይደለም።  በኢሕአፓ የተነሳ እንሞታለን። ካስፈለገም እንገላለን። የሆነው ይሄ ነው። ዛሬም ድረስ የኢሕአፓ ፍቅራችን በውስጣችን ነዶ ያላለቀው፣ ከማንነታችን ጋር ባለው የጠነከረ ትስስርና በጊዜው ስለ መጭው ዓለም በሰጠን ተስፋ ነው።

በኢሕአፓ  የተስፋ ዓለም ውስጥ ሁሉም ነገር ውብ ነው። ችግር የሚባል አይታሰብም። ሰዎች ያቅማቸውን ሰርተው የፈጉትን ያህል ይወስዳሉ። የመደብ፣ የብሄር፣ የጾታ ጭቆና አይኖርም። የገጠርና የከተማ ልዩነት ይጠፋል። የአይምሮና የጉላልበት ሥራ የሚባል  ልዩነት የለም። ዓለም አንድ ትሆናለች። የሰው ልጆች በፍቅር እና በሰላም አለም አቀፋዊነትን ይዘምራሉ። ወደ ተሰፋዋ ውብ ዓለም መድረሻው መንገዱ ኢሕአፓ ብቻ ነው። ስለዚህም በኢሕአፓ ድርድር የለም።

የሕይወት ተፈራን መጽሀፍ ሳነብ አንድ የገረመኝ ጉዳይ፣ በእዚያን ጊዜ ከጌታቸው ጋር የነበራት የግል ግንኙነት ነው። ዛሬ ላይ ሆኘ ሳስበው ምንም ማለት አይደለም። በዚያን ጊዜ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ይሄን የሰማሁት ግን በጣም ያስደነግጠኝ ነበር። እኔ በማውቀው ኢሕአፓ ሴት ጓዶቻችንን በምንም መልኩ የከጀለ፣ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባት የፈለገ ብቻ ነው። ለምን? የኢሕአፓ ሴት ጓዶች የተለዩ ናቸው። ማንም እንደ ሌላ ሴት ሊያቸው አይችልም። ይሄም ለኢሕአፓ ከሰጠነው የከበረ ትርጉም የመጣ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ተግባራዊ ችግርም ነበረው። በግል ስሜት ውስጥ የገቡ ሁለት ወጣቶች ለኢሕአፓ ያላቸው ስሜት ይቀንሳል፣ የሚል ስጋት ነበረን። ከዚህም አልፎ በግል ስሜታቸው ስጓተቱ የደርግ ደህንነቶች ሰለባ የሆኑም ነበሩ። ይህ ሁኔታ ደግሞ መዘዙ ከእነሱም አልፎ ለሌሎቻችን ይተርፋል። አደገኛ ነው።

ሕይወት በመጽሀፏ ያነሳችው በድርጅቱ ውስጥ የተነሳውን የሀሳብ ልዩነትና ልዩነቱም ለማስተናገድ የተሞከረበት መንገድ የሚል ጉዳይ አለ። በቅርቡም እርሷም በተገኘችበት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ምሁራኖች፣ በእሸቱ ጮሌ አዳራሽ፣ ስብሰባ ላይ ይሄ ጉዳይ ተነስቶ  እንደነበር አንድ ዘገባ አንብቤ በጣም ገረመኝ። ምክንያቱም በጊዜው የነበሩ የኢሕአፓ መሪዎች በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር የፈቱበት መንገድና በተለይ ደግሞ ጌታቸው ስለ ችግሩ አፈታት የነበረው አመለካከት፣ በኋላ ከደረሰበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ እጅግ  የተለያዬ አመላካከት የነበራቸው መሪዎች እንደነበሩ ተደርጎ የቀረበው ጉዳይ ነው።

ያን ጊዜ አይደለም ዛሬም ያለው የሀገሪቷ ምሁር በስነልቦና መሰረት ጉልተኛነት ነው። የጉልተኛነት ስነልቦናዊ መገለጫው ደግሞ ማንሀለኝነትና አትንኩኝ ባይነት ነው። ለዚህም ምክንያት አለው።

በሀገራችን  ዘመናዊ ምሁርን የፈጠረው የትምህርት  ሂደት በማህበረሰቡ እድገት ፍላጎት ጋር በተያያዘ ሂደት ሳይሆን በጊዜው የነበሩ የሀገሪቷ መሪዎች፣ አንድም ካለማወቅ፣ ሌላም ፈረንጅ ሀገር ሲሄዱ ያዩትን ስልጣኔ ባቋራጭ ለማምጣት የነበራቸው ጉጉት ያስከተለው ችግር ነው። የሀገራችንን ምሁር ህብረተሰቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሂደት የወለደው አይደልም። ያ ሂደት ገና በእንጭጩ እያለ በውርጃ የተፈጠረ ምሁር ነው። ለእዚህም ነው ዛሬ ድረስ ቅጡ የጠፋው። በአለም በታወቁ ታላላቅ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ተምሮ የመጣው ምሁር፣ እቤቱ ውስጥ የልጆቹንና የሚስቱን ድስት ለይቶ ለብቻው ለመብላት የሚዳዳው። ለእዚህም ነው ምንም ዓይነት የዘመናይነት አሻራ በማህበረሰቡ ላይ ማሳረፍ ያልቻለው። በባህሉ፣ “ተራ” ከሚባለው የሕብረሰተሰብ ክፍል ጋር ልዩነት የለውም። በራሱ መሀከል የሚነሳውን ችግር በውይይትና በሰለጠነ መንገድ ሊፈታ  አልተቻለውም። ይሄን ጉዳይ የፈለግነው ያህል ሽፋን እንስጠው እንጂ፣ እውነታው ይሄው ነው። ይህ ደግሞ በፖለቲካው ውስጥ ባለው ምሁር ላይ ብቻ ያለ ችግር አይደለም።

የኢሕአፓ  ምሁራን የግራ ምሁራኖች ናቸው። የፈጠራቸውም በውርጃ የተጀመረው የሐገሪቷ የምሁር ፈጠራ ሂደት ነው። ኢሕአፓን ጨምሮ የግራው ምሁር የዚህ  የውርጃ ሂደት ሁለተኛ ውርጃ ነው። በኢሕአፓ  ውስጥ የነበሩት ዓባላትም ሆኑ አመራሮች በትምህርታቸው የተጉ ብሩህ ዓይምሮ የነበረቸው ነበሩ። ይዘው የመጡት የፖለቲካ ፕሮግራም ግን ቅድም ስላልኩት የውርጃ ሂደት የሚለው ትልቅ ጉዳይ አለ። በወቅቱ በአንድ ጊዜ ተነስቶ ፣ እግዚአብሄር የለም። እንዴት? ካርል ማርክስ፣ እግዚአብሄርን የፈጠረውን ሀይማኖት የፈጠሩት የገዥ መደቦች ናቸው። ምክንያቱም ተገዥውን አደንዝዘው ለመግዥ  ዘዴ እንዲሆናቸው ነው። ሀይማኖት የብዙሀኑ ሕዝብ ማደንዘዣ እጽ ነው። ብሏል፣ እኛም ተቀብለናል። ታሪክ የሚባል ነገር የለም። ያለው ታሪክ አንድ ነው፣ የሕዝቦች የመደብ ትግል  ታሪክ ነው። ንጉሱ የሉም፣ እግዚሀብሄር መረጠኝ ስላሉ እግዚአብሄር ከሌለ እሳቸውም የሉም፣ ሀገርም ጊዚያዊ ነው፤ ለምን? ዓለም የላብ   ደሮች ስለሆነች፣ ላብ አደሮች ደግሞ በመከሀላቸው የሀገር ድንበር እያበጁ  ገደብ የሚያስቀምጡበት ምክንያት የላቸውም። ሀይማኖት ከሌለ ፓትራያርኩም ኢማሙም የሉም። የሚል ፓለቲካ በአንድ ጊዜ ይዞ  ነው፣ ኢሕአፓ  የመጣው።  ይሄ ሁሉ የፖለቲካ እይታ ከማርክስ ወደ ሌሊን፣ ከሌኒን አዲሱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት የሚል  ቅጂ ይዞ  ከመጣው ሊቀ መንበር ማኦ፣ ከዚያም ወደ እኛ ሲገላበጥ አራተኛ የካርቦን ቅጅ ሆነ።

በዚህ የካርቦን ቅጂ ፖለቲካ ውስጥ ነው ሕይወት በመጻሀፏ ያነሳቸው የአንጃ መፈጠር መከራከሪያ፣ የከተማ ትጥቅ ትግል የገጠር፣ ፋሽስት በድርጊት ወይስ በንድፈ ሀሳብ፣ የሚል ጭቅጭቅ የተነሳው።  ይህ ጭቅጭቅ ደግሞ በሰለጠነ መንገድ ሳይፈታ ቀረ የሚል ትችት፣ በቀደም ከእሷ  ጋር የተሰበሰቡት ምሁራን እንደ ትልቅ ቁም  ነገር ከስንት ዓመት በኋላ ያነሱት። ሕይወትም ጌታቸውን “የኔ ጀግና” ነው፣  ያሰኛት በጊዜው በዚህ ጭቅጭ ወቅት ያሳየው የተለሳለሰ ባህሪ ነው፣ ተብሎ ሲቀርብ በጣም ገረመኝ።

ኢሕአፓን እንደ ፖለቲካ ሀይል ብቻ ወስዶ በዚያን ጊዜም ይሁን አሁን ባሉት መመዘኛዎች ለመለካት መሞከር አግባብ አይደለም። የኢሕአፓ ፍቅራችን፣ የተፈለገውን ዋጋ ለመክፈለ ዝግጁነታችን ፣ በጊዜውም የተከፈለው ከፍተኛ ዋጋ እንዴትና ለምን ተከፈለ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልሱ፣ በአራተኛ ካርቦን ገልብጦ ባመጣው የፖለቲካ ፕሮግራሙ፣ ወይም ደርግን ፋሽስት ማለቱ፣ የቦናፓቲዝምና የፋሽዝም  ንድፈ ሃሳባዊ ትነተና  አይደለም። ከላይ ልገልጸው እንደሞከርኩት ፣ በወጣትነት እድሚያችን የሰጠን የማንነት ዋጋና የነገረን የተስፋ ዓለም ነው። ለዚህም ነው በጊዜው የተደረጉ የግራ ፖለቲካ ትንተናዎች ላይ የሚደረጉ ክርክሮች ዋጋ የሌላቸው።

ኢሕአፓ ከፈለገ ምንም ማድረግ ይችላል። በየትኛውም ህግን ደንብ ሊገዛ አይችልም። በጊዜው የከተማው ትጥቅ ትግል ለምን አጓጊ እንደነበር ማሰብ አይችግርም፣ ለምን? ኢሕአፓ ከማንም ጋር፣ በየትም ቦታ፣ በተፈለገው ዘዴ፣ ቢገጥም ማንም ሊያቸንፈው አይችልም። ስለዚህ ገጠር ሆነ፣ ከተማ፣ ጧዋት ሆነ ማታ፣ ምን ልዩነት አለው። ኢሕአፓ የደረሰበት ምህታታዊ ደረጃ፣ በውጭ ላለው አይደለም፣ በውስጡ ለነበርነውም የሚገርም ነበር። ጭለማን ተገን አድረገን የሰራነው ሥራ፣ በቀን እንደሌላው ሰው እያየን የምንደነቅበት ሁኔታ ነበር። እራሳችንን የተለየን አድርገን ነበር የምናየው፣    ስለዚህ በተለያዩ የፖለቲካ  ጉዳዮች ዙሪያ የተደረጉ  ክርክሮች በራሳቸው ያመጡት ችግር የለም። ችግሩ የመጣው ከእነዚህ ክርክሮች  በስተጀርባ ሊሰተናገዱ የሞከሩት የለዘብተኛ ስሜቶች ናቸው።

ዋናው ቁም ነገር ኢሕአፓ ከማንም ጋር መዳራደር አይችልም። የተፈጠረበትም ማህበረሰባዊ ሁኔታ ይሄን አይፈቅድም። እኛም በጊዜው የነበርነው ወጣቶች አንፈቅድም። ለምን?  ንጽህናው ይጎድፋል። እግዚአብሄር የለም፣ ዘውድ የለም፣ ሀገር የለም፣ ታሪክ የለም ብለን ፣ ከተገላገልንና ከፍተኛ  ዋጋ ከከፍልን በኋላ፣  ከማንም ጋር አንደራደርም። የኢሕአፓም መሪዎች መንፈስ ይሄ ነበር። ለእዚህም ነው የጌታቸው ማሩ ሕይወት ተፈራ በመጽሀፏ የጠቀሰችው የትንተና “ዕውቀት” ትርጉም ያልነበረውም፣  የተባለውም “ዕውቀት” ለሌሎቹ የኢሕአፓ መሪዎች የተሠወረ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም። ከዚህ “ዕውቀት” በስተጀርባ የሚመጣው የመለሳለስ ሁኔታ ግን በጊዜው አደገኛ ሊሆን እንደሚችል፣ በእርግጠኝነት መናገር  እችላለሁ።

በዚያን ጊዜ በአራተኛ ቅጅ አብዮት ማካሄድ ይቻላል ብሎ የተነሳ ቡድን ፣የተከሰተውን ችግር በዘመናዊ የሰለጠነ መንገድ አልፈታውም ብሎ ማለት ፣ ያኔ አይደለም ዛሬም እንኳን የነበረውና ያለውን ሁኔታ አለመረዳት ነው። በእኔ እይታ ያኔም ይሁን ዛሬም ቢሆን፣ የምሁሩ የጉዳዮች አረዳደም ሆነ አያያዝ ችግር ምንጩ የሚቀዳው ከተፈጠረበት የውርጃ ሂደት ጉዳጓድ ነው። የግራው ምሁር ደግሞ ሁለተኛ ውርጃ ነው። በነገራችን ላይ፣ ዛሬ በሀገራችን የበላይነት ያገኘው ብሄረተኛ ሀይል የዚሁ ሂደት ሶስተኛ ውርጃ ነው። ከግራው ፖለቲካ ውስጥ ደግሞ  ብሄርተኝነት የተባለ ጉዳይ አለ። ይሄም በደካማነቱና በጭካኔው ከሚታወቀው ጆሴፍ ስታሊን ጋር የተገናኘ ንድፈ ሀሳብ ነው። ለዚህም ነው ሶስተኛ ውርጃ ያለኩት። እንደነ ኢሕአፓ ያለው የግራ ምሁር  ድርጅት  ያስጀመረው የግራ ፖለቲካ ሂደት ሶስተኛ ውርጃ አስከተለ። ዛሬ ይሄ ውርጃ  ነፍስ ዘርቶ  በብሄረተኛነትዘረኝነት ተደራጅቶ፣ ሀገሩን እያመሰው ይገኛል።

እንግዲህ ያሳያችሁ፣ ሕይወት ተፈራ በመጻህፋ ላይ ያነሳቻቸው የፓለቲካ ጉዳዮች፣ ደርግ ፋሽስት ነው ወይስ ቦንአፓርት፣ የሦስተኛ አለም የአብዮት ትግል ንድፈ ሃሳብ የከተማ ትግል ይፈቅዳል? አይፈቅድም? የብሄራዊ ግንባር ጥያቄ? የጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት ጥያቄ ታክቲካዊ ነው? ወይንስ ስትራቴጂያዊ? በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተወልዶ በአደገ የግራ ምሁር መሀከል የተነሳ ክርክር፣ ክርክሩ  የተነሳባት እጅግ አደገኛ በሆነ የደህንነት ሁኔታን ታሳቢ ስናደረገው እንዴት ሁኖ ነው? እገሌ ጥፋተኛ ነው፣ ይሄኛው ለስላሳ ነበር፣ ይሄኛው ሁኔታውን በደንብ አይቶታል፣ ያኛው አላየው፣ ማለት የሚቻለው? አስቸጋሪ ነው። እንዴውም በሀገሪቷ ውስጥ ዘመናዊ ከሚባለው ምሁር አፈጣጠርና እድገት ጋር ተያይዞ  ያለውን መሰረታዊ ችግርና ኢሕአፓ የተፈጠረበትን ማህበራዊ ሁኔታ፣ ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ሲሞከር ያለውን አስቸጋሪነት ከመፍራትም የመጣ ነው ። በቀደምም በሕይወት መጽሀፍ ሰበብ የተሰበሰቡትም ምሁራን ያደረጉት ይሄንኑ አስቸጋሪ ፍተሻ መሸሽ ነው።

ጌታቸው ማሩ የተሰዋው ተስፋዬ ደበሳይ ከፎቅ ላይ እራሱን ወርውሮ ከተሰዋ ሦስት ወራት በኋላ ነው። በእነዚህ ሦስት  ወራት ውስጥ  በአዲስ አበባ ብዙ ወጣቶች ተሰውተዋል። የቀረው ቢቀር ለሜይ ዴይ ሰልፍ ወጥተው በአንድ ማታ የተገደሉትን ወደ 1000አንድ ሺ ያህል ወጣቶች ማሰታወስ ይበቃል። በእርግጥም በእነዚህ ሶስት ወራት ውስጥ  ነፍስ የገደል ላይ ቄጤማ ሆናለች። ጧዋት ወጥቶ  ማታ ለመመለስ ምንም አይነት  ዋስትና የለም። ውስጥ ውስጡን ብዙ ነገር ይወራል። በድርጅቱ ደህንነት ላይ አንጃዎች ስጋት ፈጥረዋል፣ ይባላል። ጌታቸው ከፍተኛ አመራር ውስጥ የነበረ ነው። ብዙ ሚስጥር ያውቃል። ጓድ “ለ” በሚል ስያሜ ከአመራርነቱ ተገልሏል። ከተማው ውስጥ ነው ያለው። ሕይወትም በመጽሀፏ እንዳለችው በዚህ ወቅት ውስጥ በተደጋጋሚ በግል ታገኘው ነበር። ከዚህ በኋላ በነበረው ሁኔታ ያጋጠመው የመጨረሻ እጣ ለምን ይገርማል? ዛሬ ላይ በተለየ ሁኔታ ውስጥ  ሆነን ስናስበው ሊዘገንነን ይችላል። ሕይወት በጌታቸው ጋር የነበራት የግል ግንኙነት የፈጠረው ስሜት ያሳደረው ጫና ካልሆነ በቀር፣ በዚያን ጊዜ በከተማው የነበረው ታሪክ አንድ ነው። መሰዋት፣መሰዋት፣መሰዋት፣ የሚገበረውም የደም መረቅ ነበር፣ ሌላም አልነበረም።

ሕይወት በመጽሀፏ ላይ ከፍተኛ 19 ታስራ በነበረችበት ጊዜ ወጣቶቹ እስረኞች ያሳዩት የማግለል ስሜት፣ እሷ ብዙ መጽሀፍ አንብባ ከምታቀው የ”መንጋ” ስነልቦና HERD MENTALITY የመጣ አይደለም።  ወጣቶቹ ነፍሳቸው የሚነግራቸውን ነው ያደረጉት። ኢሕአፓ ያቸንፋል ብለው ሲሞቱ ፣ አንድ ቀን የኢሕአፓ በትግል ሁሉኑም  ጥሎ ድል ሲያደርግ እየታያቸው አይደለም። የሚሉት እኛ ኢሕአፓዎች ነን፣ ልንቸነፍ አንችልም። ወይም ኢሕአፓ ነኝ ልቸነፍ አልችልም፣ ሞትም እንኳን ቢሆን ሊያቸንፈኝ አይችልም፣ ከሚል የውስጥ ስሜት የመነጨ  ነው። በጊዜው ከፍተኛ 19 እስር ቤት ውስጥ ከሕይወት ጋር የነበሩትም አመራር የተባሉት ሰዎች ፣ እነዚያ ወጣት ፊት በአካል ተነስተው፣ በኢሕአፓ ውስጥ እኮ ሌላም አመለካከት ነበር፣  ብለው ለእስረኞቹ መናገር ምን ያህል ለወጣቶቹ ከፍተኛ መርዶ እንደሚሆን ካለማሰብ የመጣ ችግር ነው። ወጣቶቹ “መንጋዎች” ሆነው አይደለም። ሆኖም ግን በዚያን ወቅት “መንጋው” ቢበተን  የሚመጣውን አደጋ ስለሚያውቁት ነው። ይሄን የሚነግራቸው  ነፍሳቸው ነው፣ መጽሀፍ አይደለም።

ሕይወት በመጸሀፏ  እንዳለችው በእዚያ እስር ቤት ውስጥ ሁሉም ከመነጋው ውስጥ ይውጣና እራሱን መሆን ይጀምር እንበል። የዚህ ሁኔታ ሊያመጣው የሚችለው መዘዝ ቀላል አይደለም። እራሱን ሆኖ ማሰብና መወሰን ከጀመረ የሚያቀውንም የማያውቀውንም፣  ፈልጌ ነው፣ በግሌ ነው የወሰንኩት፣   እያለ የፈለገውን መናገር ቢጀምር፣ ስንት ሰው  ከእዚያ እስር ቤት ውስጥ  ሊተርፍ የሚችለው?  እንዲህ ባለ ከፍተኛ ዋጋ በሚያስከፍል ድርጅት ውስጥ ገብቶ እኔ የሚባል ነገር የለም። ያለው  አንድ ነገር ነው፣ እሱም ኢሕአፓ ነው። ኢሕአፓ ደግም በነፍስ መዋጮ የተገነባ ድርጅት ነው። የሚያስከፍለውም የመጨረሻውን ዋጋ ነው። ከመሪዎቹ ጀምሮ ብዙዎችም ሲከፍሉ አይተናል።  ከዚያ ውጭ ማሰብ ግን መሰረታዊ ውሉን መሳት ስለሆነ አደገኛ ነው። ሕይወትም ከጌታቸው ጋር የነበራት የግል ግንኙነት ያለ ቦታውና ሁኔታው የሆነው ለዚህ ነው።

ለእኔ  ሕይወት ተፈራ  በከፍተኛ 19 ታስራ በነበረችበት ጊዜ በግሏ ለተሰማት ጉዳይ የሰጠችው ክብደት በሌላ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ትክክልም፣ የሚገባም ነው፣ እላለሁ። በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ግን  እንደፈለግነው በግል እያሰብን የሚመቸንንያመንበትን የምንልበትና የምንደርግበት ድርጅት አልነበረም፣ ኢሕአፓ። የጥንካሪያችን መሰረቱ  የጋራ ማንነታችን ነው ። ዛሬም እንኳን ተነስተን በግላችን እንደልባችን ልንሆን አንችልም።  ምክንያቱም በጋራ ለተከፈለው ዋጋ ከፍተኛው እጅ የከፈሉት ጓዶቻችን አብረውን ስሌሉ፣ ያለ እነሱ ስምምነት የገባነው ውል ልናፈርሰው ሰለማይገባ ነው።

በተለይ ሕይወት  ከዚያ ሁሉ ጉድ ወጥታ በህይወት መትረፋን ፈጣሪዎ ለሁለተኛ ጊዜ እድል ስለሰጣት እንዳመሰገነች በመጽሀፏ ላይ አንብቤአለሁ። ይሄን ያህል አክብዳ የምታየው ህይወቷ የተረፈው፣ ዛሬ እሷ “ለመለኮት” ምስጋና  ታቅርብ  እንጂ፣  እኔ እስከማውቀውና እስከሚገባኝ ድረስ፣ የብዙ ጓዶቻችን የነፍስ ዋጋ የጠየቀ ጉዳይ ነው። እኔም  እስከ መጨረሻው ትንፋሻቸው ድረስ በፈላ ዘይት እየተጠበሱ ጠንከረው የቆሙ ጓዶቼ በከፈሉት ዋጋ ነው፣  እየተነፈስኩ ያለሁት። ይሄ ደግሞ ተረት ተረት አይደለም።

በእኔ እይታ ሕይወት በኢሕአፓነቱ ያገኘችውን ጌታቸው ማሩ ጋር የነበራት ግንኙነት ቀስ በቀስ  ወደ ግል  ስላደገ ፣ ከዚያ በኋላ በግል ግንኙነቱ በፈጠረው አጋጣሚ ባወቀችው ሌሎች ሁኔታዎች ላይ ተንተርሶ “የኔ ጀግና” የሚል ስያሜ መስጠቷ አግባብነት የለውም። በዚያን ጊዜ በግራም በቀኝም የወደቁ ጓዶቻችን በሙሉ ጀግኖቻችን ናቸው። ጌታቸው እንደሌሎቹ በትግል እንደወደቁት ጓዶቻችን የሕይወት ተፈራ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ጀግና ነው። ይሄንንም የምለው ለእኔ ኢሕአፓ ያለው ትርጉም ፣ በውስጡ ተነሱ በተባሉት የመስመር ልዩነቶች ከዚያ ጋር ተያይዞ በመተከሰቱ ውጣ ውረዶች ብቻ የሚለካ ስላልሆነ ነው። መለካትም የለበትም፤ ያን ለማድረግ ከሞከርን ቀደም ብዬ በጠቅላላው በሀገራችን ምሁር አፈጣጠርና በሀገሩ እና በእራሱ ላይ ያስከተለውን  ውስብስብ ችግሮችና ያ በሺዎቹ የረገፈውን ወጣት ከኢሕአፓ ጋር የነበረውን ግንኙነት   አቃሎ ማየት  ስለሚሆን ነው።

ከዚህ ሁሉ ከፍተኛ ዋጋ ካስከፈለው ታሪካቻን የምንማረው ቁም ነገር፣ በተለይ ምሁሮች የተባልን እራሳችንን በቅጡ መፈተሽ እንዳለብን ነው። በጉለተኝነት ማንነት የተለወሰውን ዘመናዊነታችን ፊት ለፊት ልንጋፈጠው ይገባል። የውርጃው ዘመን ማብቃት ይኖርበታል። እራሳችንንም ሆነ ማህበረሰባችንን ነጻ ማውጣት  ከፈለግን ውስጣችንን በደንብ መፈተሽ ይኖርብናል። ታሪካችንንም በተገቢው መነጸር ማየት ይኖርብናል። ዛሬም እንደ ትላንቱ በውሰት ባገኘናቸው መመዘኛዎች እገሌ እንዲህ ነበር፣ አሁንም ነው፣ የምንል ከሆነ፣ መከራችንና ችግራችን ይበዛል፣ ይረዝማል። የኢሕአፓንም ጉዳይ ስንመለከት ድርጅቱን ውስጥ በተካሄድ ክንውኖች ብቻ ሊሆን አይገባም። አልፎ ተርፎ ወደ ግለሰቦች ማውረድ ደግሞ የበለጠ ውሉን ያስተዋል።

ኢሕአፓን የፈጠረውን ሀገራዊና ማህበራዊ ሁኔታን በደንብ መረዳት እጅጉኑ ይጠቅማል።  ሕይወት ተፈራ በመጽሀፏ ላይ ያነሳችውን፣ እዴት የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር ስተት ሊሰራ ይችላል? ለሚለውም አስቸጋሪ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ የሚገኘው፣ ኢሕአፓን እንደ አንድ የፖለቲካ  ድርጅት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ  ማህበራዊ ክስተት ለማየት ከቻልን ብቻ ነው። በእኔ እይታ ከፖለቲካ ሰውነቱ በላይ ማህበራዊ ትርጉሙ ኢሕአፓን በበለጠ ይገልጸዋል እላለሁ። በዚህ ጽሁፍ በመአከላዊነት ልገፋ የሞከርኩትም ሀሳብ ይሄንኑ ነው። በኢሕአፓና በወጣቱ መሀከልም የነበረውን ግንኙነት ልገልጽ የሞከርኩትም ከፖለቲካው ይልቅ በጊዜው  የነበረውን  ማህበራዊ ሁኔታ መሰረት አድርጌ ነው።

ኢሕአፓ በከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ድርጅት ነው። በኢሕአፓ ጉዳይ ላይ የምንሰራው ስህተት የተከፈለውን ዋጋ ከንቱ ስለሚያደርገው ኪሳራው ከፍተኛ ይሆናል። በደንብ ከተረዳነው ግን እጅግ ሊጠቅመን ይችላል። እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ በኢትዮጵያ የፖለቲካ የድርጅት ታሪክ ውስጥ ኢሕአፓን የሚያክል ድርጅት ኖሮ አያውቅም። ይህ አባባል እውነት ነው። ግን እውነቱ በሌላ ሁኔታ ውስጥ የምናቀው እውነት አይነት አይደለም። ምክንያቱም የሀገሪቷን ምርጥ ልጆች አሰልፎ፣ አይክፍሉ ዋጋ ከፍሎ፣ ካሰበው ሳይደርስ ቀረ። ለምን? በመልሳችን ላይ  ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።

በመጨረሻም፣ እንደ ሕይወት ተፈራ የኢሕአፓነትን ታሪክን ማስነበብ ይጠቅማል፣ ነገር ግን የኢሕአፓ ጉዳይ ከአንድ ዓባል የግል ተመክሮና ግንዛቤ በላይ ስለሚሆን፣ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለሕይወት ተፈራ ለአስነበበችን ኢሕአፓነት ታሪኳ በድጋሚ ምስጋናዬ ይድረሳት፣



ከሰላሙ ባላይ b.selame@aol.com
 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com