ደራሲያን በፊደል ማውጫ
   
 
 
መሪራስ አማን በላይ
[1943 - 2009]
የደራሲው ሥራዎች
1.   ጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክ(ታሪክ)
2.   መጽሓፈ አብርሂት(ታሪክ)
3.   መጽሐፈ ፈውስ(መንፈሳዊ)
4.   መክስተ ምስጢር ሕይወታዊ ርእዮት(መንፈሳዊ)
5.   መጽሐፈ ሱባኤ ዘበአማን ካልዕ(መንፈሳዊ)
6.   መጽሐፈ ብሩክ(መንፈሳዊ)
7.   መጽሐፈ ክቡር(መንፈሳዊ)

ስለደራሲው በጥቂቱ
መሪራስ አማን የተወለዱት መጋቢት ፳፫ ቀን ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. አፕሪል 1 ቀን 1951 ዓመተ ምህረት) ሲሆን፣ የትውልዳቸው ስፍራቸው በለሳ ተብሎ በሚጠራና ጎንደር ውስጥ በሚገኘ አካባቢ ነበር። የአደጉትም በጎንደር እና በጎጃም ውስጥ ነበር ከልጅነታቸው ጀምሮ ትምህርታቸውን የቀሰሙት ከአባታቸው ከመምህር በላይ ድሉ፣ ከአባ ጼሄማ በጎንደር ተክለኃይማኖት፣ ከመሪጌታ መንክር ደብረኤልያስ ጎጃም፣ ከመሪጌታ ጉባኤ በጎጃም ነበር።

መሪራስ አማን፤ ቅዳሴን፣ ቅኔን፣ ዜማን፣ ብሉይን፣ ሃዲስን፣ የእንጨት አዋጅን (የመድኃኒት እጽዋትን)፣ የሃረግ ስዕልን፣ የኢትዮጵን ታሪክ፣ አቡሻህርን (ባህረሃሳብን) እና ሌሎችንም በአድባራት እና ገዳማት የሚሰጡ የኢትዮጵያ ትምህርቶችን ተምረዋል። በለተይ በቅኔ፣ በግስ ርባታ እና ሰዋሰው ችሎታቸው በመምህራኖቻቸው እና የትምሀርት ባልንጀሮቻቸው ስማቸው የተጠራ ነበር። በዚህም ምክንያት በጎጃም በይስማ ደጀን በመሪጌታ መንክር ዘንድ ቅኔ አስነጋሪ ነበሩ።

ተማሪ ሳሉ እና ትምህርታቸውንም ካጠናቀቁ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተዘዋወሩ አያሌ ገዳማትን እና አድባራትን እየጎበኙ በውስጣቸው የአሉትን ምስጢራዊና ጥንታዊ መጻሕፍቶቻችንን ለመመርመር እድል አግኝተዋል።

የ19 ዓመት ልጅ ኹነው ወደ ኑብያ (ሱዳን) ተጉዘው በነበረበት ወቅት በአንድ በፈራረሰ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክተርስቲያን ቅጥር ግቢ በተቀበረ የድንጋይ ሳጥን ውስጥ፣ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉ የኢትዮጵያን ታሪክ ጨምሮ ስለተለያዩ ጉዳዮች የሚዘረዝሩ በግዕዝ የተጻፉ የብራና መጻሕፍትና ጥቅሎች አግኝተዋል። እነዚህን መጻሕፍት ያገኙት የዛሬ 50 ዓመት አካባቢ ነበር። መጻሕፈቱ በግዕዝ የተደረሱ ነበሩ። በእነዚህ መጻሕፍት ላይ ተመርኩዘው ይዘታቸውን እያሳጠሩ ከ24 ያላነሱ መጻሕፍትን አሳትመው፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን በእውቀትና በጥበብ አንጸዋል።

መሪራስ አማን በላይ መጽሐፍ ከማንበብና ከመጻፍ በላይ ሌላ ሕይወት አልነበራቸውም። በራሳቸው የተመዘገቡት የመጻሕፍቱም ዝርዝር የሚከተሉት ናቸው።

1. ምዕራፈ ሕያዋን ቃለ ሕይወት ዘወንጌላውያን የምሳሌው ምስጢር በሐተታና በትንተና
2. የጥንትዋ ኢትዮጵያ ትንሳዔ ታሪክ
3. የሱባ ቋንቋ መዝገበ-ቃላት
4. መጽሐፈ ብሩክ (ብሩክ ዣንሽዋ)
5. መጽሐፈ ክቡር
6. መጽሐፈ ሱባኤ ዘበአማን ካልእ
7. መጽሐፈ አብርሂት
8. መክሰተ ምስጢር
9. መጽሐፈ እንቆአእባን
10. መጽሐፈ ሠረገላ ታቦር
11. መርሐ ጽድቅ ወአሚን ወመርሐ ግብር
12. መጽሐፈ ፈውስ
13. መጽሐፈ አድህኖት
14. ብርሃነ ሕይወት ዘበአማን
15. መጽሀሠይፈ ኃይማኖት ተዋህዶ
16. ሕይወት እንደገና በሦስት ዐለሞች
17. በአንድ ሰውነት የሦስት አካላት ምስጢር
18. መጽሐፈ ኤልያስ ነቢየ እግዚአብሔር
19. የእውነትን ሕይወት ውደዱ
20. አፍሪ-ካሁን
21. ጥበብ ከእውቀት ትምህርት ከልጅነት
22. የልቤ ወዳጅ የሰው ዘር ልጅ
23. ጸሎት አሚን ዘበአማን ወጸሎተ ተዋህዶ
24. ምክር ከእኔ ስማ አንተ ወገኔ

መሪራስ አማን በላይ፣ በሀገር ፍቅር የሚነዱ፣ ለኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ቀናኢ፣ ለኢትዮጵያ እውነተኛ ታሪክ መገለጥና መዛመት የሚተጉ እና በፍቅረ ንዋይ ያልተነደፉ ትልቅ ጠቢብ ነበሩ። ጥበብን ለአገራቸው ሕዝብ ለማቅሰም ወደኋላ አይሉም ነበር። ለአገራቸው እስከዛሬ ካበረከቱት በላይ ገና ብዙ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቢያቅዱም የማይቀረው ሞት ቀደማቸው። ይህም በመሆኑ፣ ራሱ የእውቀት ዩኒቨርሲቲ የሆነ አንድ ትልቅ ሰው ኢትዮጵያ አጥታለች።

የተከበሩት ባለታሪክ፣ ፈላስፋ፣ ባለመድኃኒት፣ የነገረ-መለኮት አዋቂ እና የ24 መጻሕፍት ደራሲ የነበሩት መሪራስ አማን በላይ ባደረባቸው ሕመም የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 17 ቀን 2017) በሎስ አንጀለስ ከተማ በተወለዱ በ65 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ምንጭ ኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ
   
   
       
 
   
     
       

መጸሐፍ ለመዋዋስ መመዝግብ ያስፈልጎታል። ለመመዝገብ እዚህ ይጫኑ

ተመዝግበው ከሆነ እዘህ ይጫኑ
     
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com