ደራሲያን በፊደል ማውጫ
   
 
 
ገብረክርስቶስ ደስታ
[1924 - 1973]
የደራሲው ሥራዎች
1.   ዐፅምና ፈለጉ(ተውኔት)

ስለደራሲው በጥቂቱ

‹‹ሞት እንደሁ ልሙት፣ በሴኮንድ መቶኛ ፣
እንቅልፍ እንደሬሣ፣ ዘለዓለም ልተኛ፡፡
… መንገድ ስጡኝ ሰፊ ስሄድ እኖራለሁ
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ፡፡
የሌለ እስቲፈጠር የሞተ እስቲነቃ
በትልቅ እርምጃ ከመሬት ጨረቃ
ከጨረቃ ኮከብ
ካንዱ ዓለም ወዳንዱ
ስጓዝ እፈጥናለሁ
በፀሐይ ላይ ቤቴን ጎጆ እቀልሳለሁ፡፡
. . . መንገድ ስጡኝ ሰፊ
ፀሐይ ልሁን ፀሐይ
እንደ ጽርሐ አርያም ሁሉንም የሚያሳይ
እሳተ ገሞራ አመድ እረመጡን
ጎርፍ የእሳት ጎርፍ ልሁን፡፡
… መንገድ ስጡኝ ሰፊ››


በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበረው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ ‹የጠፈር ባይተዋር›› ሲል 1961 ከገጠመው እጅግ ‹ሮማንቲክ› እና ጥልቅ የጠቢብ መንፈሱን ከሚገልጽለት ቅኔው የተወሰደ ነው።

ለማስታወስ ያህል ሠዓሊና ባለቅኔው ገብረክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ህዋ ላይ በተለይ ‹‹አብስትራክት›› የተሰኘውን ዘመናዊ የሥዕል አሠራር ስልት በስፋት ከማስተዋወቅ በላይ የሀገሪቱን እና የሕዝቧን ሕይወት /ባመዛኙ አጽም በአጽም በሆኑ ሥዕሎቹ በመግለጽ፣ የጠቢብና የዜግነት ገዴታውን በመሥዋዕትነት ጭምር የተወጣ ታላቅ ሰው ነበር፡፡

ድንቅ ሥዕሎቹንም በሀገርና በውጭ ሀገር በግልና በቡደን በተደጋጋሚ ያሳየ ሲሆን፣ በሕዝቦች የባሕል ልውውጥም በየጊዜው የኢትዮጵያ የሥነጥበባት ቡደን መሪ ልዑክ በመሆንም በልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ አደባባዮች ላይ ሀገሩን የወከለ የጥበብ ሰው ነበር፡፡ ለቡድንና ለግል የሥዕል ኤግዚቢሽን ትርኢቶችም /አንዳንዶቹን በድጋሚ/ ጀርመን፣ ዩጎዝላቭያ፣ ግሪክ፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ቼኮዝላቫኪያ፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ብራዚል፣ ስፔን፣ ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅግ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ ወዘተ… ረጅም ጉዞ የፈፀመ ሲሆን፣ በዘመናዊ አሣሣል የጥበብ ስልቱ በሀገሩ ብኩርናን ከማግኘት አልፎ ለዓለም የሥነ ጥበባት ባሕልም አንድ የግሉና ልዩ የሆነ መለዮውን ያበረከተ፣ ሀገሩንና አህጉሪቱን ጭምር ያስጠራ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር፡፡

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ዕድገት አርአያ በመሆኑ በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት የሀገሪቱን ከፍተኛና ዓለም አቀፋዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት በአድናቆት ተቀብለው ሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ እንደ መምህርነቱም ከ1955 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ባሉት 12 ዓመታት ውስጥ ዛሬ ለሀገሪቱ አንቱ የተሰኙ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሠዓልያን አፍርቷል፡፡ ‹‹ሞዴል አርቲሰትና መምህር›› በመሆኑም በ1963 እና 1964 ዓ.ም ከወቅቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒሰቴር እንዲሁም ከአዲሰ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤቶች ጽሕፈት ቤት የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በ1969 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ለፈፀመው ታላቅ የማስተባበር ተግባር ከዘመቻው መምሪያ የወርቅ ሜዳልያ ተሸልሟል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ግጥም በሕልም ውስጥ ገብረክርስቶስ ደስታ ራሱን የቻለ ሀተታ ነው፡፡ ገብረክርስቶስ በሕይወቱ ሳለ አንዳንድ ግጥሞቹ እና ቅኔዎቹ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ታትመው የወጡለት ሲሆን፣ አንዳንዶቹንም በልዩ ልዩ መድረኮች በሀገር እና በውጭ ሀገር ጭምር ራሱ አንቧቸዋል፡፡ እንደዘመናዊ ሥዕሎቹ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ የሥነግጥም ባህልም ውስጥ ገብረክርስቶስ ሀዲስ ዘር የዘራ የሀገራችን ዘመናዊ ግጥም ቆርቋሪ ነበር፡፡ ግጥሞቹ/ ቅኔዎቹ/ በሀዲስና በአንግድነታቸው ከጥቂቶቹ ተቃውሞ ቢያተርፍበትም በብዙዎቹ አድናቂዎቹ ተፈቃሪ ነበሩ፡፡

ገብረክርስቶስ ደስታ ወደ 60 ያህል የሚጠጉ ግጥምና ቅኔዎቹን ትቶልን አልፏል፡፡ ግለኛና አዳዲስ የአሰነኛኘት ዘዴ በመከተል በኢትዮጵያ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ አዲስ ንቅናቄ የፈጠሩ ግጥሞቹ እና ቅኔዎቹ የአማርኛ ቋንቋን ጣዕምና ለዛ ግልጽና ቀላል በሆነ፣ ነገር ግን ቅኔያዊ ውበትን በተጎናፀፈ የገለጻ ኃይል እስከ ባህላዊው ትውፊታችን ድረስ በመዝለል የኢትዮጵያውያንን ‹ነፍስ› የተገለፁ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን መልክአ ምድራዊ ገጽታ ከመቅረፃቸውም በላይ፣ ለሀገሩ ባህለኛነቱንና ወገን ወዳድነቱን ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ስብእናውን አሟልተው የገለጹለት ናቸው፡፡

ከቀደምቱ የ‹‹እማ ኢትዮጵያ አርመኛ ባለቅኔዎች›› ከነዮፍታሔ ንጉሤ፣ ከእነ ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ እና ከነዮሐንስ አድማሱ ‹‹መዝሙረ ኢትዮጵያ›› ቅኔዎች በአርአያነቷ አቻ የምትሆነው የገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹ሀገሬ›› /1951/ ዛሬ ያለምንም ማዳነቅ የብዙዎቹ ፍቁረ ኢትዮጵያን የነፃነት ሴማ ነች፡፡ እንኳን በሕይወት ካሉት፣ በሕይወት ከተለዩን መሀል አውቁ የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁሩና ሀያሲ ሥዩም ወልዴ፣ እውቁ የሥነ-ሥዕል ሊቅ ዶ/ር አሸቱ ጮሌ ወዘተ. . . ዛሬም በዐፀደ ነፍስ ሆነው/ በሕይወት ሳሉ እንደሚያደርጉት/ ‹‹ሀገሬ››ን በአርምሞ የሚያዜሟት ይመስለኛል፡፡

አብዛኛው የጥበብ ቤተሰብ በቅርብ እንደሚያውቀው በዚህች ሀገር የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ወስጥ አንዳች አሻራ ጥሎ ያለፈው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ በተለይ ካለፈው አንደ አሥርዕት ዕድሜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን መድረኮች ሲወሳ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ያለፈው ገብረክርስቶስ ደስታ ከነበሩን በርቅዬ የጥበብ ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ ይሁንና በዘመነ ደርግ፣ በሕይወቱ ላይ ባንዣበበ አደጋ በመስከረም ወር 1971 ሀገሩን በስደት ጥሎ እንደወጣ ቀረ፡፡ ከተሰደደ ከሁለት ዓመታት እንግልት በኋላ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም. በተወለደ በ49 ዓመቱ አሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ሕይወቱ ዓለፈች በወቅቱ አስከሬኑ ጭምር ‹ሀገር የከዳ› ተብሎ ለሀገሩ መሬት ሳይታደል ግብዓቱ መሬቱም እዚያው ተፈፀመ፡፡

ይህ የሕይወቱን ትራዤዲያዊ ፍፃሜ አስመልክቶ ዛሬ በሕይወት የሌሉትና ተቆርቋሪው የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሁር ሥዩም ወልዴ ‹የሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ግጥሞች› /1981/ በሚለው ዝክረ ጽሑፋቸው እንዲህ ደምድመውታል፡፡

. . . የገብረክርስቶስ ሞት ተራ የአካል ሞት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሞቱን ትራዤዲያዊ የሚያደርገው አንድ ቁም ነገር በግጥሞቹ ውስጥ እናገኛለን፡፡ . . . በተለያዩ ግጥሞቹ ውስጥ ተመልሶ እስኪረግጣት የሚናፍቃት፣ እኔም ከእናንተ ይበልጥ የምታክል አገር አለችኝ የሚላት፣ ሰው ከአገሩ ውጭ ሰው አይደለም ብሎ ሲተማመንባት የነበረች አገሩ፣ የሕይወቱን የመጨረሻ ሕልፈት ሳታስተናግድለት መቅረቷ ነው፡፡ እንኳ ሞቶ አስከሬኑን፣ ግድ ካሆነበት ቀፅበታዊ ትንፋሹን እንኳን በ‹‹ባዕድ ሀገር›› መተንፈስ የማይፈልገው ገብረክርስቶስ በ1973 በኦክላሆማ ስቴት ማረፉ የሰውን ልጅ ሕይወት ወሳኝ ወቅት ጣጣ የሚያስታውስ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፡፡

በሕይወት ካሉትም መሀል-ዛሬ በአሜሪካ /ሚኔሶታ/ ነዋሪ የሆነው፣ ዘመነኛው እና እጅግ አድናቂ የጥበብ ባልንጀራው የ‹‹ልጅነት›› እና የ‹‹ወለሎ ወለሎታት›› ባለቅኔ ሰለሞን ደሬሣ የዛረ ሁለት ዓመት ገደማ ሀገር ቤት መጥቶ በመነበረ ጊዜ ለ ‹‹ሪፖርተር›› መጽሔት /ቅጽ2 ቁ. 13 መስከረም 1991/ ስለዚሁ ስለገብረክርስቶስ የመጨረሻ እጣ የገለፀው እንኳን የወዳጆቹን የማንኛውንም ልብ የሚሰብር ነው፡፡

. . .ለኢትዮጵያውያን ፀሐፊዎችና ሠዓሊዎች ችግር ይደርስባቸዋል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ደረሰበት፤ መጨረሻው ላይ ስለ አወጣጡ የሰማሁት ነገር አለ፡፡ እሱን አላጣራሁምና አልደግመውም፡፡ ችግር ደርሶበት ወጥቶ ታሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አንድም ኢትዮጵያዊ በሌለበት ማንም በማያውቀው ሀገር ኦክላሆማ በተባለ ቦታ ሞተ፡፡ አሜሪካ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ እኔ ያለሁት ሜኔሶታ እሱ ያለው ኦክሎሆማ ነበር፡፡ ብሰማና ባውቅ ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ ሲሞት የሚያውቀው ፊት እያየ ይሞት ነበር፡፡ አሁን ሳስታውሰው በጣም ሆዴን ይበላኛል፡፡

ሙሉ ታሪኩን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ምንጭ:ብርሀነ መስቀል ደጀኔ ‹‹የጠፈር ባይተዋሩ›› አሌፍ መጽሔት የተወሰደ።

የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥሞች ለማንበብ እዚህ ይጫኑ [አምሀ አስፋው፣ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ እና አማረ ማሞ አሰባስበው እንዳቀረቡት።]

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እና ከ የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጦች ተገልብጠው የተተየቡ የገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች [መስከረም 1947 - ነሐሴ 1961]
በፈቃደ አዘዘ
   
   
       
 
   
     
       

መጸሐፍ ለመዋዋስ መመዝግብ ያስፈልጎታል። ለመመዝገብ እዚህ ይጫኑ

ተመዝግበው ከሆነ እዘህ ይጫኑ
     
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com