አንዲት የ18 ዓመት ጉብል ከዐንድ ዐይታው ከማታውቀው ወጣት ጋር ልትገናኝ ትወጣለች። ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ ያጋጠሟትና ያለፈችባቸው ተከታታይ ክስተቶች በሕልሟም ፣ በዕውኗም አይታው/አስባው በማታውቀው ሁኔታ ሕይወቷን ግልብጥብጡን አውጥተው ይለውጡታል። ማማ በሰማይ የፍቅር ታሪክ ነው። የአብዮትም፣ የተስፋም፣ የሕልምም፣ የአመፅም፣ የሽብርም፣ የመተማመንም፣ የመከዳዳትም፣ የሰቆቃም፣ የሰቀቀንም፣ እራስን በራስ የመለወጥም፣ የድል አድራጊነትም፣ የነዚህ ሁሉ ሰብዓዊ ረቂቅ ባሕርያት ታሪክ ነው። መጽሐፉ፣ ደም የጠማው ወታደራዊ ጁንታ ባቀጣጠለው ታይቶ የማይታወቅ የጅምላ ጭፍጨፋ ሃገሪቱ በሞላ የተወራጨችበት፣ ተሰምቶ የማይታወቅ ቁጥር ያለው ህዝብ - በተለይ ወጣቱ - እንደ ቅጠል የረገፈበት የኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ወቅት ቅልብጭ ያለ ሥዕል ነው። በታሪክ ውስጥ ብቅ ብለው ከጠፉት እጅግ ጨካኝ አምባገነን ሥርዓቶች አንዱ በሆነው ላይ በመነሣትና በቁርጠኝነት በመጋፈጥ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ ለማኅበራዊ ፍትሕና ለሰብዓዊ ክብር የታገሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ታሪክም ነው።
|