አንድ ጭብጥ የቴምር ፍሬዎች

ዋና ገጽ | ልብ ወለድ
+ - Font Size  
 
 

አንድ ጭብጥ የቴምር ፍሬዎች

  


ድርሰት በጣይብ ሳሊህ
ትርጉም ኤፍሬም ተሰማ

በወቅቱ በጣም ጨቅላ ሳልሆን አልቀረሁም፡፡ እድሜዬ ምን ያህል እንደነበር በውል ባላስታውስም ከአያቴ ጋር የሚያዩኝ ሁሉ እራሴን እያሻሹ ጉንጬን ሲደባብሱኝ ይታወሰኛል፡፡ እነዚህ በአያቴ ላይ የሚሞከሩ ማሞካሻዎች አልነበሩም፡፡ የሚደንቀኝ ነገር ቢኖር ከአባቴ ጋር የትም ቦታ አልሄድም ነበር ይልቁንም ቁራን ለማጥናት በመስጊድ ከማሳልፈው ማለዳ በስተቀር በቀሪው ጊዜ የሚሄዱበት ሁሉ የሚወስዱኝ አያቴ ነበሩ፡፡ ወንዙ መስጊዱና ለጥ ያሉት ሜዳዎች የእለት እኩዮቼ የሆኑ ህፃናት መስጊድ ሄደው ቁራን ለመቅራት ባለመፈለግ ሲንጫጩ እኔ ግን ለቁራን ትምህርት የማይበርድ ፍቅር ነበረኝ፡፡ ምክንያቱም ያለምንም ጥርጥር ምዕራፎቹን በቃሌ ፈጥኜ ለመያዝ በመቻሌና ሼኹ ጎብኚዎች በመጡ ቁጥር ቆሜ መሃሪው ከሚለው ምዕራፍ በቃሌ እንዳሰማ ስለጠየቁኝ ጎብኚዎቹም ከአያቴ ጋር ሲያገኙኝ ሌሎች ሰዎች እንደሚያደርጉት እራሴን ስለሚደባብሱኝ እና ጉንጬን ስለሚያሻሹኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በእርግጥ ለመስጊድ ልዩ ፍቅር ነበረኝ፡፡ ወንዙም የደስታዬ ምንጭ ነበር፡፡ የማለዳ የቁራን ጥናቴን ስጨርስ የእንጨት ሰሌዳዬን አሽቀንጥሬ ወደ እናቴ እነደጂኒ በመብረር ቁርሴን በፍጥነት ጎራርሼ ወደወንዙ በመሮጥ ዘልዬ እገባበት ነበር፡፡ መዋኘቱ ሲታክተኝ ከወንዙ ዳርቻ አረፍ ብዬ እየተሰባበረ በመጠማዘዝ የሚፈሰው ውሃ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ታጥፎ የግራር ዛፎች ከሞሉበት ደን ኋላ ግዙፉን መንገዶች እንደሚኖሩ በማሰብ ደስታ አገኛለሁ፡፡ እነዚህ ግዙፍ ሰዎች ልክ እንደ አያቴ ረዣዥምና ቀጥ ያለ አፍንጫ እንዲሁም ነጭ ሪዝ እንዳላቸው በምናቤ እስላለሁ፡፡ አያቴ የማዥጎደጉድላቸውን በርካታ ጥያቄዎች ከመመለሳቸው አስቀድሞ ሁሌም የአፍንጫቸውን ጫፍ በአመልካች ጣታቸው ጢማቸውን እንደሚያደርጉት ሁሉ ያሻሻሉ፡፡

ሪዛቸው ለስላሳ እጅብ ብሎ የበቀለ እና እንደ ጥጥ የነጣ ሲሆን በሕይወቴ ሙሉ እንዲህ ዓይነት ፍፁም ፀአዳ ወይም የተዋበ ነገር አላየሁም፡፡ እያቴ በጣም ረዥም ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ምክንያቱም በአካባቢያችን ማንም ሰው ወደ ላይ ሳያንጋጥጥ ሊያናግራቸው ሲሞክር አላየሁም፡፡ ደግሞም ወደ ቤት ውስጥ ሲገቡ በጣም ሳይጎነብሱ የገቡበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ማጎንበስ ብቻ ሳይሆን ጎብጠውና ተጠማዘው ወደ ቤት ሲገቡ በምናቤ የግራር ደኑን አልፎ በመጠማዘዝ የሚያልፈውን ወንዝ እስላለሁ፡፡ በጣም ስለምወዳቸው ሳድግ ረዥም ደልዳላና ከፍተኛ ግርማ የሚራመድ ዓይነት ሰው እንድሆን እመኛለሁ፡፡ 

ከልጅ ልጆቻቸው መካከል ለእርሳቸው ከምንም የበለጠ ተወዳጅ መሆኔን አምናለሁ፡፡ ይህም አያስገርምም ሌሎቹ ዘመዶቻችን የማይረቡ ደነዞች ሲሆኑ እኔ ግን ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ ብልህ ልጅ በመሆኔ ነበር፡፡ አያቴ መቼ እንድስቅና መቼ ደግሞ ፀጥ እንድል እንደሚፈልጉ አውቃለሁ፡፡ በተጨማሪም በጸሎት ሰዓት የሶላት መስገጃ የሚሆን ውሃ ማጠራቀሚያ ውስጥ እሞላለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ያለምንም ጉትጎታ አከናውናለሁ፡፡ በእረፍት ጊዜያቸው ውበት በተላበሰ ቅላፄ ቁራን ስለቀራላቸው በደስታ ያዳምጣሉ ልባቸው መነካቱንም ከፊታቸው ገጽ ላይ አነባለሁ፡፡ 

አንድ ቀን ስለ ጎረቤታቸው ስለማሱድ አያቴን እንዲህ በማለት ጠየቅኋቸው ‹‹የኛን ጎረቤት ማሱድን የሚጠሉት ይመስለኛል?›› የአፍንጫቸውን ጫፍ እያሻሹ መለሱልኝ ‹‹አበያ የሆነ ሰው ነው እኔ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን አልወድም›› አያቴ ለጥቂት ጊዜ አቀረቀሩ ከዚያም ፊት ለፊታችን ወደተዘረጋው ሲፊ ሁዳድ አይናቸውን አቅንተው እንዲህ አሉኝ ይታዩኛል ከበረሃው ጫፍ እስከ አባይ ዳርቻ ድረስ የተመሰረተውን ሁዳድ ታያለህ አንድ መቶ ፌደን ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ የቴምር ዛፎች ታያለህ? እነዛስ ዛፎች ማዶ ላይ ይታሁሃል? ስንት ግራር ታያለህ ይህ ሁሉ ማሱድ እቅፍ ውስጥ ሊገባ የቻለው አባቱ አውርሶት ነበር፡፡ 

አያቴ በዝምታ ሲዋጡ አጋጣሚውን በመጠቀም እይታየን ከሳቸው ላይ በማንሳት በሰፊው ሁዳድ ላይ አሳረፍኩት፡፡ 

‹‹ይህ ለኔ ምንም ማለት አይደለም›› ለውስጤ ነገርኩት፡፡ 

እነዚህ የቴምር አዝመራዎች እነዛ ዛፎች ወይም ይህ ጥቁር የተሰነጣጠቀ መሬት የማንም ቢሆን ግድ የለኝም፡፡ የማውቀው ነገር ቢኖር የህልሜ ሰገነት የምፈነድቅበት መስክ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ 

ከዚያም ንግግራቸውን ቀጠል በማድረግ ‹‹አዎ የኔ ልጅ የዛሬ አርባ አመት ሁሉም የማሱድ ንብረት ነበር፡፡ አሁን ሁለት ሶስተኛው የኔ ሆኗል›› አሉኝ፡፡ ለኔ አዲስ ዜና ነበር፡፡ ቀድሞም ቢሆን አምላክ መሬትን ከፈጠረ ጀምሮ ይህ መሬት የአያቴ መሆኑ ነበር የሚሰማኝ፡፡ 

‹‹በዚህች መንደር ዱካዬ ባረፈበት ጊዜ አንድ ፊደን አልነበረኝም፡፡ የዚሁ ሁሉ ሲዳይ ባለቤት ማሱድ ነበር፡፡ ዛሬ ሁኔታውን ተለውጧል ወደፊት ቢሳካልኝ አላህ ወደ እቅፍ ሳይጠራኝ በፊት ቀሪውን ሲሶ ወደራሴ ማስገባት እፈልጋለሁ፡፡›› 

ምክንያቱን ባላውቅም ከአያቴ የወጡት ቃላት አስፈራሩኝ፡፡ እናም ከጎረቤታችን ለማሱድ ሀዘኔታ ተሰማኝ፡፡ እያቴ ምኞታቸውን ሳይፈጽሙ ቢቀሩ ምንኛ ጥሩ ነበር የማሱድ እንጉርጉሮ የድምጹ ማማርና እንደወራጅ ውሃ የሚያስገመግመው ሳቁ ታወሰኝ፡፡ 

አያቴ ፈጽሞ ስቀው አያውቁም፡፡ ማሱድ ለምን መሬቱን እንደሚሰጥ ጠየቅኋቸው፡፡ ‹‹ለሴት!!›› የሚለው ቃል አንድ አስፈሪ ነገር ያለበት መሆኑ ተሰማኝ፡፡ ‹‹ማሱድ እኮ የኔ ብዙ ያገባ ሰው ነው፡፡ ባገባ ቁጥር አንድ ወይም ሁለት ፌደን መሬት ይሸጥልሃል፡፡ 

ማሱድ ዘጠና ያህል የሚደርሱ ሴቶች ማግባቱን ለቅጽበት ያህል አሰላሰልኩ፡፡ ነገር ግን ሦስት ሚስቶች የተጎሳቆለው ማንነቱ አንካሳ አህያው ከተበጣጠሰ ኮርቻዋ ጭምር፡፡ እንዲሁም እጅጌው የነተበው… ጀለቢያው… እነዚህ ሁሉ ታወሱኝ ሰውየው ወደኛ እየቀረበ ሲመጣ በአዕምሮዬ የታጨቀው ሃሳብ ሁሉ በነነ፡፡ 

ከአያቴ ጋር ለቅጽበት ተያየን፡፡ 

‹‹ዛሬ ቴምሩ ይሰበሰባል›› አለ ማሱድ ‹‹እዛ መምጣት አትፈልግም እንዴ?›› በማለት ቢጋብዛቸውም አያቴ በቦታው እንዲገኙ አለመፈለጉ ተሰማኝ፡፡ አያቴ ግን ከተቀመጡበት ተስፈንጥረው ሲነሱ ዓይናቸው ለአንድ አፍታ ኃይለኛ ብርሃን ሲረጭ ተመለከትኩ፡፡ እጄን እየጎተቱ የማሱድ ቴምር ወደሚሰበሰብበት ስፍራ ወሰዱኝ፡፡ 

አንድ ሰው ለአያቴ ዱካ አመጣላቸው፡፡ ዱካው የበሬ ቆዳ ጣል ተደርጎበታል፡፡ እኔ ግን ባለሁበት እንደቆምኩ ነበርኩ፡፡ በስፍራው በርካታ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእያንዳንዶቹ በቀር ሁሉንም አላውቃቸውም እዚያ መገኘቴ ማሱድን ለማየት ስላስቻለኝ አልከፋኝም፡፡ የሚሰበሰበው ቴምር ንብረቱ እንዳልሆነና በዚያ የሚደረገው ማናቸውም ነገር እንደማይመለከተው ሁሉ ለብቻው ፈንጠር ብሎ ቆሟል አንዳንዴ ትልቅ የቴምር ቅርንጫፍ ከአናት ተገንጥሎ መሬት ሲያርፍ የሚያሰማው ድምጽ ከሄደበት ሀሳብ የሚመልሰው ይመስላል፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ከቴምሩ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ተቀምጦ በረዥምና ስለታም መቁረጫ ለጋዎቹን ቅርንጫፎች ለሚመለምለው ልጅ ጮህ በማለት ‹‹የቴምሩን ልብ እንዳትቆርጠው ጠንቀቅ እያልክ!›› አለው፡፡ የተናገረውን ነገር ከቁብ የጣፈው አልነበረም፡፡ ከቴምሩ ዛፍ ጫፍ ላይ የተቀመጠው ወጣት ለጋውን ቀንበጥ መዘንጠፉን በመቀጠል ኃይልና ፍጥነቱን ጨመረ፡፡ ለጋዎቹ ቀንበጦች ከሰማየ ሰማያት እንደሚወረወር አንዳች ነገር ወደ መሬት ማመማቸውን ቀጠሉ፡፡ እኔ ግን የማሱድን አባባል እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ የቴምር ዛፍ ልብ ስሜት ያለው የሚመታና ደም የሚረጭ መሆኑን በማሰላሰል ተጠበብኩ፡፡ አንድ ቀን በአንድ የቴምር ዛፍ ቀንበጥ ስጫወት ማሱድ አግኝቶኝ የተናገረውን አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹የኔ ልጅ የቴምር ዛፍ እኮ ልክ እንደ ሰው ነው፡፡ ሀሴትና መከራ ይፈራረቁበታል፡፡›› እናም በዛ ጊዜ አንዳች የህፍረት ስሜት ተሰማኝ፡፡ 

በድጋሚ ፊት ለፊት ወደተንጣለለው ሜዳ ተመለከትኩ፡፡ በእድሜ እኩዮቼ የሆኑ ሕፃናት በቴምር ዛፎች ዙሪያ እንደጉንዳን እየተርመሰመሩ ግሬውን ይለቅማሉ፡፡ አብዛኛውን ወደአፋቸው ይልኩታል፡፡ የተሰበሰበው ቴምር ትልቅ የፍሬ ቁልል ሆነ፡፡ ሰዎቹ ተሰብስበው በመስፈሪያ እየሰፈሩ ወደ ዶንያ መክተት ያዙ፡፡ ሰላሳ ብቻ ቆጥሬ ታከተኝ፡፡ ሁሴን ነጋዴው ከኛ መሬት ቀጥሎ በስተምስራቅ አዋሳኝ መሬት ያለው ሙሳ ቀድሞ ከማላውቃቸው ሁለት ሰዎች በቀር ሌላው ሰው ሁሉ በየአቅጣጫው ተበታተነ፡፡ 

ዝቅተኛ የፍጨት ዓይነት ድምጽ ሰማሁ፡፡ አያቴ ለካ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወስዷቸው ኖሯል፡፡ ማሱድ ቀድሞ ከነበረበት አልተንቀሳቀሰም ከቀድሞው የሚለየው ነገር ቢኖር አፉ ውስጥ የሆነ ነገር ማኘኩ ነበር፡፡ ሁኔታው ከምግብ ጋር እንደተጣላና የጎረሰው ምግብ ምን እንደሚያደርገው እንዳላወቀ ሰው በአፉ ውስጥ ያንገዋልለዋል፡፡ 

አያቴ ድንገት ከእንቅልፋቸው በመንቃት ተፈናጥረው በመቆም በዶንያ ሞልቶ ወደተደረደረው ቴምር አመሩ፡፡ ነጋዴው ሁሴን ወሰንተኞችና ባለመሬቱ ሙሳ ሁለቱ እንግዶች ሰዎች አያቴን ተከተሏቸው፡፡ በዶንያው ዙሪያ በመቆም የቴምሩን ፍሬ እየዘገኑ መመልከት ያዙ፡፡ እያንዳንዶቹ አንድ ሁለት ፍሬ ወደአፋቸው ሲወረውሩ አያቴ አፈስ አድርገው ሰጡኝ፡፡ ወዲያው ማኘክ ጀመርኩ ማሱድ ግን አፍኜ ሙሉ ያፈረሰውን የቴምር ፍሬ ወደ አፍንጫው በማስጠጋት አሸተተው፡፡ መልሶም ዶንያው ውስጥ ከተተው፡፡ ከዚያም ዶንያዎቹን እርስ በእርሳቸው ተከፋፈሉአቸው፡፡ ነጋዴው ሁሴን እስር ወሰንተኛችን ሙሳ አምስት የኔ አያት ደግሞ አምስት ዶንያዎች ወሰዱ፡፡ 

‹‹ግራ እንደተጋባሁ ወደ ማሱድ ስዞር ሁለቱ ዓይኖቹ መንገድ እንደጠፋባቸው አይጦች ሲቅበዘበዙ ተመለከትኩ፡፡ 

‹‹ገና ሃምሳ ፓውንድ ብር እንዳለብህ አትዘንጋ?›› አሉት የኔ አያት፡፡  

‹‹ስለሱ በኋላ እንነጋገራለን›› 

ሁሴን ነጋዴው ረዳቶቹን ጠርቶ አህዮቹን አስመጣ፡፡ ሁለት እንግዳ ሰዎች ግመሎች ስላመጡ በዶንያ የነበረውን ቴምር ግመሎች ላይ ጫኑ፡፡ ከአህዮቹ አንዷ ስታናፋ ግመሎች አረፋ በአፋቸው እንደፈቁ ድመጽ በማሰማት አፋደሱ፡፡ 

የልብሶቹን ጫፎች መነካት እንደፈለግሁ ሁሉ ወደማሱድ እየቀረብኩ እጆቼን ወደ እርሱ ስዘረጋቸው ተሰማኝ፡፡ የሚታረድ በግ እንደሚያሰማው ያለ ማንቆረር ድምጽ ከጉሮሮው ሲወጣ ሰማሁ፡፡ ደረቴ ላይ ሀይለኛ የስቃይ ስሜት ቀስሮ ያዘኝ ሩጫዬን በረጅሙ ለቀቅሁት አያቴ ከኋላ ሲጣሩ በመስማቴ ጥቂት አመንትቼ ነበር በኋላ ግን ፍጥነት ጨምሬ ተፈተለኩ በዛ ቅጽበት እንደጠላኋቸው ተሰማኝ ፍጥነቴን ስጨምር ከውስጤ አውጥቼ ልጥለው የፈለኩት ዓይነት ምስጢር የተሸከምኩ ይመስለኝ ነበር እወንዙ ዳር ከግራሩ ጫካ አጠገብ ፈረሰኛው ውሃ ከሚጠመዘዝበት መታጠፊያ ጣቴን ጉሮሮዬ ውስጥ በመስደድ የበላሁትን የቴምር ፍሬ አስወጣሁት፡፡ 


እፍታ 100 ትረካዎች 1993 ዓ.ም
 
ይህን አጭር ልብ ወለድ ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com