የካቲት 12 ቀን

ዋና ገጽ | ልብ ወለድ
+ - Font Size  
 
 

የካቲት 12 ቀን

  


ተመስገን ገብሬ

ኢጣሊያኖች በኢትዮጵያውያን ላይ ስላደረጉት ጭካኔና የአረመኔነት ሥራ ከመናገር፤ ጠቅላላውን ለታሪክ ትተን፤ መራራ የሆነ የትንግርት ታሪካዊ ሕይወት ለእያንዳዱ በዚያ ቀን ተሰጥቶታልና የሊቀ ጠበብት እውነቱን ሕይወታቸውን እንመልከተው።

እርሳቸው አጭር፤ ጠይም፣ ዓይናቸው ደካማ፣ ግራጫ ጢም ያላቸው፣ ወፍራም፣ ዕድሜያቸው ገፋ ያለ ሰው ናቸው።

ኢጣሊያኖች ከለኮሱት ከመንደሮቹ የቃጠሎ እሳት የተነሳ ጊዜው ለማየት ድግዝግዝ ያለ ነበር። ከብዙ ሰዎች ጋር ከመንደራቸው ተጎትተው ከመጡ በኋላ ፀጥ ብለው ከኢጣሊያኖች ሞትን ብቻ ይጠብቁ ነበር። ሊቀጠበብት እውነቱ ዓይናቸውን ከፍተው ዙሪያቸውን ተመለከቱ ነገር ግን ፈዝዘው ነበር። በሩቅ የተመለከቱ ሻካራ የሆነው የወጨጫ ተራራ ሰማያዊ መስሎ በሩቅ ታያቸው፤ ጦም ነበርና ተርበው ነበር። ከወደ ኋላ በኩል ደግሞ ቤታቸው እየነደደ ቀርቷል።

ከአንድ ካሚዎን ላይ አንድ የኢጣልያን ኦፊሰር ወረደና ቀበቶውን ጠበቅ አድርጎ እየቆለፈ መጣ። አጠር ያለ ለግላጋ ባለባበሱ ያማረበት ሰው ነው። የመለዮው ቆብ ወደ ግንባሩ በኩል አጋድሎ ማዕዘናዊ የሆነ ስስ ጥፍጥፍ ነው።

በትልቅ ጩኸት “ከዚያ ያሉት ስንት ናቸው” ብሎ ኦፊሰሩ ጠየቀ። ድምፁም የሚስፈራራ ነበር።

ሰርጀንት የሆነው ሹም ሰላምታ ሰጠና “ሰባ ናቸው ሲኞር ማጆሬ” ብሎ መለሰ።

ሲኞር ሜጀር በቁጣ “በጥቂት ሴኮንድ ሁሉንም እጨርሳቸዋለሁ፤ ባለ ውኃውን መትረየስ አቅርቡልኝ” አለ።

ሰርጀንቱ “ባለውኃውን መትረየስ” ብሎ እንደገና ጠየቀ፤

ስድስት ሰዎች ባለውሃውን መትረየስ ተሸክመው ከካሚዮኑ አውርደው መጡ። እነሊቀ ጠበብት እውነቱ ከቆሙበት ካቂቂ ወንዝ ውስጥ ፊት ለፊታቸው ላይ ወስደው ዝም ብለው ጠመዱት። መትረየሱም ትኩር አድርጎ የሚመለከታቸው ያህል ሆነ።

ከባዱ መትረየስ አፉ በጣም ሰፊ ነው። ከሊቀ ጠበብት እውነቱ ቀጥሎ ያለው ሰው ደፋር አይደለም። ድምፁን ከፍ አድርጎ ሊፀልይ ጀመረ፡፤ በሥላሴ ስም አማተበ። /አዐትብ ገጽየ፤ ወኩለንታየ በትምህርተ መስቀል፤ በስመሥላሴ።/ ከታጠበ ልብስ እንደተጨመቀ ያህል ላብ እንደውኃ በፊቱ ላይ ፈሰሰበት።

ሜጀሩ ወደ መትረየሱ ተራመደ። ፊቱ ልክ የሞት መልክ መሰለ። ጥይት አቀባባዩን እያስተካከለ ከመትረየሱ በኋላ ተንበረከከ። ቀና ብሎ ደግሞ ወደ ሰዎቹ ተመለከተ።

መሣሪያ ከመያዛቸው በተቀር ከተያዙት ከሰባው ሰዎች የኢጣሊያኖች ቁጥር ጥቂት ያነሰ ነበር።

“ፊታቸውን አዙሯቸው” ብሎ ሜጀሩ ጮኸ። እስረኞች ቀስ በቀስ ብለው ሲዞሩ ያቃቂን ወንዝ ፈሳሽ በፊታቸው በኩል ባንድ ርምጃ ርቀት ብቻ አዩ “አሁን አንድ እርምጃ ወደፊት ይጨምሩ” ብሎ በቁጣ ጮኸ። እጅ ለእጅ በገመድ ሰንሰለት የተያዙት እስረኞች አንድ እርምጃ ጨምረው ልክ ከውኃው ግንገን ላይ ቆሙ።

ሊቀጠበብት እውነቱ ወደፊታቸው ተመለከቱ። ተራራው፤ መስኩ፤ መሬቱም እንደ እንዝርት የሚዞር መሰላቸው። በሩቅ ደግሞ ያቃቂ መድኃኒያለምን ቤተክርስቲን ጣራውን አዩ። ይህን ሊያስተውሉ በመቻላቸው ምክንያት ዓለም በጸጥታ እንዳለ ያህል ደግሞ መሰላቸው። በድንገት ግን ለሞት ቀርበዋል።

ጫንቃ ለጫንቃ ተፋፍገው ቆመው ከኋላ በኩል ሊቀጠቡብት እውነቱ ሞት እንደደረሰባቸው ተሰማቸው። ሜጀሩም የመትረየሱን ቃታ በጣቱ ሲጨብጥ አይተዋል። አላባቸው። ልባቸውም ሊፈነዳ እስኪደርስ ድረስ በፍጥነትና በኃይል መታ። ባጠገባቸው ሙቀጫ የሚወቀጥ እንጂ፤ የራሳቸው ልብ እስከማይመስል ድረስ ነበር።

ከዚህ በኋላ ከመትረየሱ /ደመና ውስጥ/ የርሳስ ዝናም ዘነመ። መደዳውን በገመድ ተያይዘው ውኃው ሽቅብ አነሳቸው። ድንጋዮችንም ፈላለጣቸው። ካቃቂ ከፈሳሹ ወንዝ ላይም ከደም ማዕበላቸው ጋር እንደሞገድ ሆነው ገቡ።

ያቃቂ ወንዝ ለሊቀጠበብት እውነቱ ሰውነት ቀዝቃዛ ወይም የሞቀ መሆኑ እስከዛሬም አልታወቀም። የመትረየስ እርሳስ የሰበራቸው የድንጋዮች ስባሪ ፊታቸውን ሸነታትሮታል። እንደተጠፈጠፈ እንደኩበት፤ ከውኃው አሸዋ ላይ ተጣበቁ። በላያቸው ላይ የመትረየስ እርሳስ ዓየሩን እየሰነጠቀው ሲያፏጭ፤ ነፍሳቸው ትጨማደድና ትፈታ ነበር። የሚያጓራው መትረየስ ዝም አለ።

የጫማ ዱካ ወደ ወደቁበት እየቀረበ እንደመጣ ሊቀጠበብት እውነቱ ሰሙ። ከሊቀ ጠበብት እውነቱ ጥቂት ራቅ ብሎ ከወደቁ አንድ ሰው ሲያቃትት ነበር።

አንዳንድ ጊዜም እንደሚናገር ያህል ነበር። ያለውን ግን ፈጽሞ ለማስተዋል ሊቀጠበብት እውነቱ አልቻሉም። የተጋደመበትን አሸዋ በጫማ እየዳሰ ሲኞር ማጆሬ በቀረበ ጊዜ ሊቀጠበብት እውነቱ እንደገና ከደረታቸው በኩል መሬቱን አጥብቀው ተጠጉት። ቆስለው ከነበሩት ሰዎች “እባክህን ጨርሰን” ብለው መግለጽ በማይቻል በሥቃይ ድምጽ ሜጀሩን ለመኑት። ሳቀና ተዋቸው። ሊቀጠበብት እውነቱም ሲስቅ ሰሙት።

ሊቀጠበብት እውነቱ ማየት የሚችሉ በአንድ ዓይናቸው ብቻ ነበር። አንዱን አይናቸውን ደም አልብሶታል። እርሳስ የሰበረው ድንጋይ ፊታቸውን አቁስሎት ነበር። ዓይናቸው እንደሌለ ነው እንጂ፤ ምን እንደሆነ ከቶ አላወቁም። ሥቃይም የላቸውም።

ትክክል ፊታቸውን ከፍሎ ደማቸው ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ቅድም አይተውት የነበረው ተራራው፤ መስኩ፤ የአቃቂ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ይህ ሁሉ ከፊታቸው ተሠወረ። በእጃቸው የቀረው ዓለም እንደከብት በደረታቸው የተጠፈጠፉበት አሸዋ ብቻ ሆነ። ፍጹም ጸጥታ ነበረ።

ከግራ ጎናቸው በኩል ጉንዳን ወረራቸው። ሞተዋልና እንደሞቱ ሁሉም መቅረት አለባቸው። ጉንዳኖች ወደ ትኩስ ቁስል ዘመቱ።

ካዲስ አበባ ሸሽተው የሚያመልጡ አያሌ ሰዎች በሩቅ ታዩ። “ሲኞር ማጆሬ ከዚያ በኩል ብዙ ሰው ከከተማ ይሸሻል” ብሎ ሰርጀንቱ ነገረው።

በአንድ ገና ጨዋታ ላይ አንድ ግብ እንደሆነለት ወጣት በትልቅ ደስታ ወደሌላው ግብ ዞረ። ዝንጉርጉር የሆነችውን ቢራቢሮ ለመያዝ በአበባ ወራት እንደሚፈነድቅ ሕፃንም የሚገደሉ ሌላ ሰዎች ደግሞ በማየቱ ፈነደቀ። አልተከተላቸውም። ቀድሞ ሊቆያቸው በአቋራጩ ሮጦ ቀደመ። ባለውኃውን መትረየስ ተሸክመው ወታደሮች ተከተሉ።

ሊቀጠበብት ያን አንዱን ዓይናቸውን እንደገና ከፈቱት። ጫማ ብቻ አዩ። ሰው ከዚያ ጫማ ጋር አለ እንደሆነ፤ ወይም የለ እንደሆን ለማስተዋል አልተቃኑም። የሞትን ሕግ ጠበቁ። በልባቸው ውስጥ “ሚካኤል በዕለተ ቀንህ በክንፍህ ጋርደኝ” ብለው ጸለዩ።

ኳኳታ ሰሙ፤ ጫማው እየራቀ መሔዱን አዩ። ይህ አሁን የሔደው በዚያ ከነበሩት ጣልያኖች መጨረሻው ይሆናል። ጥቂት በጥቂት እየተቃኑ አስተዋሉ። ከተገደሉት በተቀር አንድም ሰው ባጠገባቸው አልነበረም። ከሞቱት መካከል ብቻቸውን ተነሱ። የታሰሩበትን ገመድ ከእጃቸው ለማላቀቅ ግራ ቀኝ ያሉትን ሬሳዎች ጎተቱ።

ወዴት ላይ እንደተመቱ ወደሞትም የሚያደርስ ቁስል አላቸው እንደሆነ ከቶ አላወቁም። ነገር ግን ለመሔድ እንደማይችል ሕፃን ተንቦራቹ። ራቅ ብሎ ደግሞ የመትረየስ ተኩስ ሰሙ። ጨለማ መሆኑ ድፍረት ሰጣቸውና ተጓዙ። በዚያ በመሐመድ ዓሊ ወፍጮ ጥግ አደሩ።

ቀኑ ሔደና ሌሊቱ መጣ። ሌሊቱ ደግሞ ሊሔድና ቀን ሊመጣ ነው። እርሳቸው ግን በሕልም ውስጥ ወይም በውን እንደሆኑ እርግጠኛ ሁነው የሚያውቁት አልነበራቸውም። አዲስ አበባ ኢጣሊያኖች በለከሱት እሳት ተቃጥላ ስትጨስ ቀን አይተው ነበር። ሌሊት ደግሞ በቃጠሎዋ ነበልባል እንደኮከብ ስታበራ አይተው አንድ ጊዜ አለቀሱ። ዕንባቸው በቁስላቸው ወረደና ፈጃቸው። ለበለባቸው። “አምላክ ቦታውንና ሕዝቡን ትቶት ሔዷል” አሉ።

ከዚያ በኋላ ጠባ። ውኃ ተጠምተው አገኙ። የአቃቂ ወንዝ ባጠገብ ነው። ትናንት እርሳቸው የተገደሉበት ወንዝ ይኸው ነበር። የሰው ደም፤ የእርሳቸውም ደም፤ ከዚያም ውኃ ጋር ሲቀላቀል ትናንት አይተዋል። ተጠምተዋልና ሲጠጡት ግድ የለም። መልሰው ደግሞ “አላደረገውም” አሉ ትናንት በተገደሉበት ውኃ ውስጥ በወደቁ ጊዜ ልብሳቸው ግማሹ ተነክሮ ነበር። ያን ጨምቀው ሊጠጡ ሞከሩ። ነገር ግን ልብሳቸውን ጨምቀው ውኃ አላገኙም። ትንንት ማታ እንደጨመቁት ረስተው ነበር።

ውኃ እንዲጠጡ ወደ አቃቂ ወንዝ ወረዱ። ሞት ከዚያ ይፈልጋቸው ይሆን፤ ወይም እርሳቸው ሞትን ፍለጋ መሔዳቸው ይሆናል። አስበውበት አዲስ አበባን በሞት መግነዝ ኢጣሊያኖች የጠቀለሉበት ምክንያት ግራዚያኒ ትናንት በቦምብ ስለተመታ መሆኑን ከእኔ ብቻ አወቁት። በዚያም እስር ቤት ውስጥ ስድስት ቀን አብረን ቆየንና ሲፈቱ ወደ ጎጃማቸው ተሻገሩ፡፤

    ከስደት ከተመለስሁ በኋላ ባለፈው ዓመት ሹመት ፍለጋ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ እንደገና ተመልሰው አይቻቼዋለሁ። አሁን የደምበጫ አለቃ መላከ ሰላም እውነቱ ተብለው ተሸመዋል።


ተመስገን ገብሬ
 
ይህን አጭር ልብ ወለድ ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethioreaders.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
lamesgin getnet [426 days ago.]
 nice

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com