ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ የካቲት 6 ቀን 1924 ዓ/ም ከአባቱ ከመምሬ ገብረ ዮሐንስ ተሰማና ከእናቱ ከወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተ ወልድ አዲስ አበባ ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ አጥቢያ ተወለደ:: ዕድሜዉ ለትምህርት ሲደርስ በዚሁ ደብር ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደግሟል:: ዳዊቱን: በቃሉ ጭምር ያውቀው ስለነበረ የዳዊት መጽሐፍ ባላገኘ ጊዜ በዓቢይ ጾም ዳዊት በሚተዛዘልበት ወቅት በቃሉ ያስተዛዝል ነበረ።
ቀጥሎም የዜማ ትምህርት ከመሪጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ወንበር ዘርግተው ከሚያስተምሩት ዘንድ ገብቶ ጾመ ድጓን ዘልቆአል:: በዚያን ጊዜ ከእየደብሩ 2:2 ልጆች እየተመረጡ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ጥሪ ስለደረሰ ከሁለቱ ተመራጮች አንዱ ሆኖ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ገብቶ በዘመናዊ ትምህርት ስምንተኛን ክፍል አጠናቅቆ ሁለተኛ ደረጃ እንዳለ ወደ ግሪክ አገር እንዲሄድ ስለተመረጠ በ1943 ዓ/ም ወደ ግሪክ አገር ሄዶ ቆሮንጦስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቋል:: እዚያ በነበረ ጊዜ ዝንባሌው ግልጽ እየሆነ ሄደ:: ፍልስፍና ትምህርት ላይ ትኩረት ስለአደረገ የፍልስፍናን መጽሐፍት በብዛት እየገዛ ያነብ ነበር:: የህ የጋለ ፍቅር እስከ መጨረሻ ሕይወቱ አልከሰመም:: የመጽሐፍ ሱሰኛ ቀበኛ እንደነበር በዚህ አደባባይ ሳልገልጠው አላልፍም:: ብዙዎቹን መጽሐፍቱን ለተመለከታቸው በእርሳስ ተዥጐርጉረው ገጾቻቸው ተበሳስከው ነው የሚገኙት:: አመለኛ ጎብኝቶአችዋል ማለት ነው::
ወደ: ነገሬ ልመለስና የቆሮንጦስን ትምህርት ቤት ሲጨርስ ንግግር እንዲያደርግ የተወሰነው እርሱ ነበር:: ንግግሩ ቅደም ተከተሉ የሠመረ ብቻ ሳይሆን ለለጋ ዕድሜዉ ጥልቅ የፍልስፍና ሐሳብን ያዘለ ነበር:: በዚያን ጊዜ በወቅቱ የአቴን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ መምህራን እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር:: እጓለ ንግግሩን ሲጨርስ አንድ የዩኒቨርስቲ መምህር ከመቀመጫው ተነሥቶ ሒዶ ስሞ አመስግኖታል::
አቴን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምህርትን ከፍልስፍና ጋር አዛምዶ አእምሮውን ያንጽ ጀመር:: ለትምህርት የነበረው ፍቅር በአርእያነት የሚጠቀስ ነበር:: የተወሰነውን የአራት ዓመታት ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ጀርመን ሀገር ሄዶ ቦን ዩኒቨርስቲ ከፍልስፍና ፉከልቲ ተመዝግቦ ያ የሚጓጓለትን ፍልስፍና ይዋኝበት ጀመር:: በዘመኑ ከቦን ዩኒቨርስቲ በዓለም መድረክ የታወቁ መምህራን ያስተምሩ ነበር:: የእነርሱን ትምህርት ሳያስታጉል በጥንቃቄ ያዳምጥ ነበር:: በግልም እያነጋገረ ስለ ፍልስፍና ትምህርት አጠናንና አቀራረብ መመሪያ ይቀበል ነበር:: ይህም አልበቃ ብሎ በሌላ ዩኒቨርስቲ አንቱ የተባሉና በዓለም መድረክ ያንጸባረቁ ለምሳሌ ፍራይቡርግ ዩኒቨርስቲ Martin Heidegger ሀይደልበርግ ዩኒቨርስቲ Karl Jaspers ያስተምሩ ስለነበር እዚያ ያሉበት ድረስ እየሄደ ትምህርታቸውን አዳምጧል:: ሁለቱም እንደሚታወቀው Existentalist Philosophers ናቸው:: የ Martin Heidegger የታወቀው ሥራ “ጊዜና መሆን” Time and Being የሚለው ምን ያህሉንም እጓለን ያረካ አልመሰለኝም የ Jaspers ን “እውነት” Von der Wahrheit የሚለውን ግን ከአንደበቱ የማይለየው ነበር: ሁሉንም ባይሆንም እንኳ አብዛኛዎቹን የዚህን ፈላሰፋ ድርሰቶች ገዝቶ ከግል ቤተ መጻሕፍቱ አከማችቶአል:: ምናልባት ወደዚህ ፈላስፋ መንፈሱ ያጋደለው ሚዛናዊና ኅላፊነት የተሞላ አስተሳሰብ ስላለው ሳይሆን አልቀረም::
ቀደም ካሉት ፈላሰፋዎች የሚያደንቃቸው አፍላጦንን ፕሌቶንና ኢማኑኤል ካንትን ነበር:: የአፍላጦን “ሪፑብሊክ” የካንትን “የንጹሕ አእምሮ ሒስ” Critique of Pure Reason የሚባሉት አዘውትሮ ደጋግሞ የሚያነባቸው መጽሐፍት ነበሩ:: ምናልባት ከመጽሐፍ ቅድስ ለጥቆ በሁለተኛ ደረጃ የሚመደቡ ሳይሆኑ አልቀረም::
የእጓለ አስተሳሰብ የተመሠረተው በሶቅራጥስ ጥያቈና ምላሽ ዘዴ ላይ ነበረ:: ስለ: እውነት ሲባል የአንድን ሐሳብ ደካማና ጠንካራ ጐን እየገመገሙ እስከ መጨረሻዉ ሂደት ማድረስ ነበር:: በምንም ዓይነት በሚከራከርበት ወቅት አይቆጣም:: የሚቆጣ ሰው እንኳን ቢያጋጥመው አለሳልሶ ወደ ጤናማ ክርክር ይመልሰዋል:: በምዕራብ አስተሳሰብ ገጸ ባሕርይና ሐሳብ የተለያዩ ናቸው ምንም እንኳን አንዱ ከሌላው ጋር የተያያዘ ቢሆንም:: ሐሳቡን መንቀፍ ሰውየውን ማዋረድ አይደለም::
ከባለ ቅኔዎች ደግሞ አሊጌሪ ዳንቴን ፤ ፍሪድሪክ ዊልሔም: ጆሴፍ ቮን ሽለርንና ዮሐንቮልፍጋንግ ቮንጌቴን በተለይ ይወዳል:: እንደ ባለቅኔዎቹ ቅደም ተከተል በዚያኑ መጠን ፍቅሩ እያየለ ይሄዳል:: ጌቴ ላይ ሲደርስ ፍቅሩ ይጠናል:: ከፊተኞቹ ሁለቱ ላይ ቀንጨብ እያደረገ በስንኝ ወደ አማርኛ ተርጉሟል:: ከዳንቴ መካነ ንስሐ ከመግቢያው ተርጉሞ ከመጽሐፉ ውስጥ ጨምሮ አሳትሞታል:: እንዲሁም ከሽለር “ዋስትና” የሚለውን ተርጉሟል:: ይበልጥ ያተኮረው ግን ጌቴ ላይ ነበር:: “ፋውስትን በሙሉ በሰንኝ ለመተርጐም አቅዶ ጀምሮ አካሂዶታል:: ነገር ግን ዳር ሳያደርሰው በሞት ተቀደመ:: እንደዚሁ በጅምር የቀሩ “ከተረት ወደ ኅሊና” የሚል የፍልስፍና ድርሰትና “መዝሙረ ኢትዮጵያዊ” የሚል የግጥም ሰብስብ ይገኝበታል:: ቀደም ሲል የካንትን ሥነ ምግባር ለማስተማሪያ እንዲያገለግል ገና ከትምህርት ቤት እንዳለ ተርጉሞታል:: እጓለ የግጥም ተሰጥዎ በተጨማሪ ነበረው:: የግጥሙ ስልት የሚከተለው ከፍ ብለው በተጠሩት ባለቅኔዎች ፈር ነበር:: ሌላው ተዘጋጅቶ አልቆለት ሳይታተም የቀረ በአንቀጸ ብጹዓን ላይ የተመሰረተ የአባቱን ምግባረ ሠናይ የሚገልጽ በመንፈሳዊና በፍልስፍና ሐሳብ የተጠናከረ ሰፋ ያለ ጽሑፍ ነው:: የዚህን መጽሐፍ ታትሞ መውጣት ለማየት በጣሙን ይጓጓ ነበር::
ቦን ዩኒቨርስቲ የዶክተር ማዕረግ ካገኘ በኋላ ምኞቱ በከፍተኛ ተቅዋም ለማስተማር ስለነበረ የማስተማርን ዘዴ ለማጠናከርና የእንግሊዝኛ ዕውቀቱን ለማጎልበት እንግሊዝ አገር በርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ ቆይቶ በ1953 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ:: ወዲያው ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመድቦ ፍልስፍናን ማስተማር ጀመረ:: በዚያን ጊዜ ነው ፍልስፍና ለበስ ንግግሮችን በተከታታይ በራዲዮ ለሕዝብ ያሰማ የነበረው:: እነዚህንም ኋላ አሰባስቦ “የከፍተኛ ትምሀርት ዘይቤ” በሚል ርእስ አዲሰ አበባ በ 1956 ዓ/ም መጽሐፍ አሳትሟል:: በዚህም በኢትዮጵያ አስተሳሰብና በምዕራብ አስተሳሰብ መካከል ድልድይ ሠርቷል:: ስለዚህ በዚህ አገር በዘመናዊ ዐዋቂዎች ታሪክ ግንባር ቀደም እንዲሆን አስችሎታል :: ከዚሁ ጋር መጥቀስ የሚገባው በአስተማሪነቱ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ራዲዮ የታወቀውን መምህር አብራራው በመባል የሚታወቀውን ፕሮግራም ስያሜውንም የሰጠ ፕሮግራሙንም የጀመረ ዶ/ር እጓለ መሆኑን ነው::
በ1956 ዓ/ም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛዉሮ በቦን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንደኛ ጸሐፊ ሆኖ ሠርቷል:: እዚያም 6 ዓመታት ያህል ካገለገለ በኋላ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ተዛውሮ በአማካሪነት ማዕረግ የክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግሏል:: በ 1965 ዓ/ም የመምሪያ ኃላፊ ሆኗል:: ከኅዳር ወር እስከ ስኔ ወር 1970 ዓ/ም በበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካሪ ሆኖ ሠርቷል:: ከጥር 1 ቀን 1972 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ጡረታ ክልል ገብቷል:: ከዚያን ጊዜ እስከ ዕለተ ሞቱ ባለው ዕድሜ ከፈጸማቸዉ ሥራዎች በኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱሰ ማኅበር አማካይነት የግዕዙን ሐዲስ ኪዳን ለማሻሻል በተቋቋመው ቡድን ያደረገው አስተዋፅኦ ጎላ ብሎ የሚታየ ነው:: ሐዲስ ኪዳንን በተለይ ጳዉሎስን በእናቱ በግሪኩ ዘር በቃሉ ጭምር የሚያውቀው በመሆኑ የእርሱ ድርሻ የላቀ እንደነበር ይገመታል::
1983 ዓ/ም እንደሚባለው ለእጓለ ጎደሎ ዓመት ነው:: ይህ ዓመት ከገባ አንሥቶ ፈጽሞ ጤና አልነበረውም:: ዓመቱ ሲጋመስ እንዲሁ ጤንነቱ ተጋመሰ:: እዚሁ አዲስ አበባ ሐኪም ቤት ገባ ፤ ግን ሕመሙ አልተሻለውም:: ለተሻለ ሕክምና ናይሮቢ ኬንያ ተላከ:: ሕክምናው አሁንም ውጤት አላሳየም:: መጋቢት 23 ቀን 1983 ዓ/ም ናይሮቢ ኬንያ ዐረፈ:: አስከሬኑ በአይሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተጓጉዞ መጋቢት 26 ቀን 1983 ዓ/ም ሥርዓተ ቀብሩ በቀራንዮ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ተፈጸመ:: ወሩ ይለያይ እንጂ ወር በገባ በ23 አባቱ ያረፉበቱ ዕለት ነው:: አባት ልጃቸውን ጠሩ ልጅም ለአባቱ ታዘዘ::
ዶ/ር እጓለ ሚያዝያ 8 ቀን 1964 ዓ/ም ከወይዘሮ እሀትአፈራሁ ተስፋዬ ጋር በቁርባን ታጋብቶ 3 ልጆችን አፍርቷል::
ቸሩ አምላክ ነፍሱን ከአብርሃም ፣ይስሐቅና ያዕቆብ እቅፍ ያኑርልን::
የቅርብ ጓደኛቸው ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ እንደጻፉት http://www.facebook.com/Dr.Eguale/info
|