ደራሲያን በፊደል ማውጫ
   
 
 
ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ
[1902 - 1996]
የደራሲው ሥራዎች
1.   ትዝታ(ታሪክ)
2.   የሕልም እዣት(ልብወለድ)
3.   የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም(ትምህርት)
4.   ኢትዮጵያ ምን ዐይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል ?(ታሪክ)

ስለደራሲው በጥቂቱ
ሐዲስ ዓለማየሁ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረማርቆስ አውራጃ ከየኔታ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ከወ/ሮ ደስታ ዓለሙ ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን፥ ለቤተሰባቸው ብቸኛ ልጅ ናቸው።

ሀዲስ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በቤተሰባቸው አጠገብ እና በአባታቸው ሀገር ደብረ ኤልያስ ሄደው ከባህላዊ የግዕዝ ት/ቤት ዜማ ተምረዋል፥ቅኔ ተቀኝተዋል።

በ1918 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የመጡት ሀዲስ፥በዚያው አመት በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለው በኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ በአዲስ አበባ በመምህርነት በጎጃም በጉምሩክ ሥራ ባለሙያነት ሠርተዋለል።

በኢጣሊያ ወረራ ወቅት 1929-1933 ዓ.ም. ከልዑል ራስ አምኃ ኃ/ስላሴ ጦር ጋር በአርበኝነት ሲዋጉ ቆይተው በምእራብ ኢትዮዽያ በጣሊያን ተማርከው፥ ወደ ኢጣሊያ በግዞት ከቆዩ በኋላ በ1936 ዓ.ም. ወደ ሀገራቸው በነፃነት ተመልሰዋል።

ከነፃነት በኋላ ዘመናዊት ኢትዮዽያን ለማደራጀት በተደረገው ትግል በማስታወቂያ ሚኒስቴር 1936፥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - በኢየሩሳሌም 1937-1939 እና በተ.መ.ድ 1939-1946፥ በእንግሊዝ 1948፥ እንደገና በተ.መ.ድ 1949-1953 ሀገራቸውን በአምባሳደርነት ያገለገሉ ሲሆን በዚሁ "ወርቃማ" የሥራ ዘመናቸው በመዲናችን አዲስ አበባ- የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ECA እንዲመሰረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደጉ ክቡር ኢትዮዽያዊ ናቸው።

ከ1953 ዓ.ም. የታኅሣሡ መፈንቅለ መነግስት ሙከራ በኋላ እስከ 1961 ዓ.ም. ድረስ በሚኒስትርነት ማእረግ በሚኒስትሮች ም/ቤት የመማክርት ጉባኤ አባል፥ ከ1961 - እስከ 1966 ድረስ በሀገሪቱ ፓርላማ የህግ መወሰኛ ም/ቤት አባል ከ1966 ጎጃም ሕዝብ በመረጣቸው መሰረት የብሄራዊ ሸንጎ አባል 1966-1968 ሆነው ያገለገሉ ሀዲስ ዓለማየሁ "ኢትዮዽያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?" 1966 በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ሀገራቸው ያላቸውን የመልካም አስተዳደር ራእይ ተመልክቶ ደርግ የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሆነው እንዲሰሩ ጠይቋቸው አለመቀበላቸው ተነግሯል።

ሀዲስ አለማየሁ በ1929 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ካዘጋጁዋት "ያበሻና የወደኋላ ጋብቻ" በኩር የተውኔት ድርሰታቸው ፋቡላ አንስቶ "ተረትተረት የመሰረት" 1948 "ፍቅር እስከመቃብር" 1958፥ ወንጀለኛው ዳኛ 1974፥ "የልምዣት" 1980 በተሰኙት የረዥም ልቦለድ ሥራዎቻቸው ያልታተሙ ድርሰቶችም አሏቸው የኢትዮዽያን ዘመናዊ ሥነጽሑፍ በአያሌው የታደጉ "የቀለም ሰው" ናቸው።

ሀዲስ ዓለማየሁ "ፍቅር እስከመቃብር" በተሰኘው የአማርኛ ረዥም ልቦለድ ሥራቸው "ለኢትዮዽያ ሥነጽሁፍ አዲስ ምእራፍ ከፋች!" የሚል ሞገስ ያገኙ ሲሆን፥ በዚሁ ኪናዊ ሥራቸውም ፋሽስት ኢጣሊያ ከወጣ በኋላ ብዚዎቹ ኢትዮዽያውያን ደራስያን ያላተኮሩበትን የፊውዳል ኢትዮዽያን ገፅታ በተለየ ትኩረት በስፋትና በጥልቀት በመዳሰስ ኪናዊ በሆነ የቋንቋ ኃይልና ውበት የገለጹ፥ በፊውዳሉ ሥርዓት ላይ ያመፁ እንደ ጉዱ ካሣ፥ በዛብህ፥ ሰብለወንጌል፥ አበጀን የመሳሰሉ ሕይዋን ገፀባሕርያት በመሳል - በለውጥ የትግል መንፈስ ላይ ለነበረው አዲስ ትውልድ ሀዲስ ራዕያቸውን በጥበብ አጋርተዋል።

በአጻጻፍ ብልሃቱ በአማርኛ ሥነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ አዲስ ፈር በቀደደው የ"ፍቅር እስከ መቃብር" ድርሰታቸው በሁለት የውጭ ቋንቋዎች ተተርጉሟል "አዲስ ዓለም አሳየን!" የሚል ሞገስ ያገኙት ሀዲስ ዓለማየሁ በ1960 ዓ.ም የቀ.ኃ.ሥ. ሽልማት ክብር በሥነጽሁፍ ነሐሴ 27 ቀን 1991 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ጽሑፍ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።

"ትዝታ" 1985 በሚለው ግለ ታሪካቸው ሰብዕናቸውን የተረኩልን ታረክ ፀሐፊ፥ አርበኛ መምህር፥ አምባሳደር፥ ሚኒስትርና የሥነ ጽሑፍ ጠቢብ ሃዲስ ዓለማየሁ "የኢትዮዽያ ሥነ ጽሑፍ አባት!" የሚል የሀያስያንና የሕዝብ ሞገስ አግኝተው ኅዳር 28 ቀን 1996 ዓ.ም. በ94 ዓመታቸው አረፉ።

ምንጭ:ብርሀነመስቀል ደጀኔ 2000ዓ.ም ብራና.ማ.ቤ ካሌንደር።
   
   
       
 
   
     
       

መጸሐፍ ለመዋዋስ መመዝግብ ያስፈልጎታል። ለመመዝገብ እዚህ ይጫኑ

ተመዝግበው ከሆነ እዘህ ይጫኑ
     
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com