ይልማ ሀብተየስ በ፲፱፴ ዓ.ም. አዲስ አበባ ተወለዱ፡፡ ይልማ በሰባት ዓመት ዕድሜያቸው የቤተክርስቲያን ትምህርት ለመቅሰም ወደ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ሄዱ፡፡ እዛም ፊደል ቆጥረው መልዕክተ ዩሐንስና ዳዊት ደግመዋል፡፡ ከዛም በ1ዐ ዓመታቸው ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት በመግባት እስከ አምስተኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ በዚህ ወቅት የሥነ - ጽሑፍ ፍላጎት አልነበራቸውም።
ከዚህ በኋላ በ፲፱፵፰ ዓ.ም. ይልማ ከጓደኞቻቸው ጋር የላብራቶሪ ቴክኒሻንነት በቀድሞ አጠራሩ ፓስተር ኢኒስቲትዩት ተማሩ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም ራስ ደስታ ሆስፒታል በመግባት በላብራቶሪ ቴክኒሻንነት ማገልገል ጀመሩ፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል ካገለገሉ በኋላ ጎንደር በሚገኘው የመግሥት ጤና ኮሌጅ በመግባት ከፍተኛ የላብራቶሪ ቴክኔሻንነት ትምህርታቸውን ተከታተሉ፡፡ ጎንደር እያሉ ነው የልብወለድ መጻሕፍትን የማንበብ ፍቅር ያደረባቸው፡፡ መኮንን እንዳልካቸው፣ ከበደ ሚካኤልንና በወቅቱ ታዋቂ የነበሩ ደራሲዎችን ያደንቁ ነበር፡፡ ከውጭም ጎርኪ፣ ዶስቶቪስኪ፣ ቶልስቶይ፣ ዲከንስ፣ ሄምንጊዌይን ያደንቃሉ፡፡
በወንጀል ክትትል ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በመጻፍ አድናቆትን ከአንባቢያን ያገኙት ይልማ፤ የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን "ያልታደለች በሰው ሰርግ ተዳረች" በ፲፱፶፭ ዓ.ም.፣ ቀጥሎም "እትዬ ላድርስሽ" ን በ፲፱፶፮ ዓ.ም. አሳትመዋል፡፡ በ፲፱፶፯ ዓ.ም. "ለወጉ ለአርባ ስምንት ሰዓት ተዳሩ" የሚለውን አሳተሙ፡፡ በተከታታይ በወንጀል ላይ ያተኮሩ ልብ ወለዶች የጻፉ ሲሆን "ሌላው እጅ"፣ "ሦስተኛው ሰው"፣ "አጋጣሚ"፣ "እሱን ተይው" ተደናቂነትን ያተረፉ ሥራዎቻቸው ናቸው፡፡
ምንጭ: የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ።
|