ገብሬ በ፲፱፲፱ ዓ.ም. በመንዝና ግሼ አውራጃ ማማ ምድር ወረዳ እምቢ ጣጣ ቀበሌ ተወለዱ፡፡ ከተወለዱበት አካባቢ በ፲፱፴፫ ዓ.ም. ለቀው አዲስ አበባ መጡ፡፡ መጀመሪያ በዓታ ከዚያም ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ገብተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ከዛም በብሪቲሽ ካውንስል የሁለት ዓመት ሥልጠና ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
በአዲስ አበባና በተለያዩ ክፍላተ ሃገራት ት/ቤቶች በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተዛውረው ዘመናዊ የመማሪያ መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፡፡
በዚሁም ከመማሪያ መጻሕፍት አዘጋጆች የምሥክር ወረቀት ተሸልመዋል፡፡ እንዲሁም በመሥሪያ ቤቱ ትምህርት ነክ በሆኑ ልዩ ልዩ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ሠርተዋል፡፡ ዕውቀትን በማሻሻል በኩል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሕግ ትምህርት ዲፕሎማ ተቀብለዋል፡፡
ገብሬ ወዳጆ ያሳተሟቸውና በ፲፱፵፮ ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ሚኒስቴር በሥራ ላይ አውሏቸው የነበሩ መጽሐፍት የፊደል መማሪያ፣ የመምህሩ መማሪያ፣ ለማና ዘመዶቹ፣ ለማ በትምህርት ቤት፣ ለማ በገበያ ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም በ፲፱፴፰ ዓ.ም. ያሳተሙት የአማርኛ ንግግር መሣሪያ ለመምህሩ መምሪያ ይገኝበታል፡፡
ምንጭ: የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ።
|