የተወለዱት ላዛሪስት ትምህርት ቤት አካባቢ ነጋድራስ ጨርቆስ ሰፈር በ፲፱፲፱ ዓ.ም. ነው፡፡ በሕጻንነታቸው ወላጆቻቸው ስለሞቱ ያደጉት ከአጎታቸው ቤት ነው። የመጀመሪያ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ላዛሪስት ሚሲዮን ትምህርት ቤት ሲሆን በጠላት ወረራ ጊዜ ጣሊያን ት/ቤት ገብተው በጣሊያንኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ ተሸንፎ ከተባረረ በኋላ ወደ እንድብር በመሄድ ለሁለት ዓመታት በፈረንሳይኛ ቋንቋ፤ ለሦስት ዓመታት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመማር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ከመጀመሪያዎቹ የሕግ ምሩቃን መካከል በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቅ የመጀመሪያው ሰው ናቸው፡፡ በንግድ ሕግ የዶክተርነት የክብር ዲግሪ ከሎንዶን ኢንስቲትዩት አግኝተዋል፡፡
“ፒኖኪዮ” በሚል ርዕስ በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈውን መጽሐፍ “አፍንጮ” በሚል ርዕስ “ላፎንቴን” ተረትና ምሳሌዎች የተካተቱበትን “ኮሬ” የተባለውን መጽሐፍ ከጣሊያንኛ “ልባሙ ልጅ” በሚል ርዕስ በሦስት ክፍል ተተርጉመዋል፡፡ “አኒማል ፋርም” የሚለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ “የእንስሳት ዕድር” በማለት ተርጉመው ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡ ከድርሰት ሥራ ወይም ከትርጉም ውጭ ልኖር አልችልም የሚሉት አቶ ለማ አማርኛ፣ ግዕዝና ጉራጊኛ፤ ከውጭ ቋንቋዎች እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና ላቲን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡
ለማ ፈይሳ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ሰርተዋል፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ መሠረት የጣሉት እሳቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ምንጭ: የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ። |