አቤ ጉበኛ በ፲፱፳፭ ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ተወለዱ፡፡ በስድስት ዓመታቸው ፊደል ቆጥረው ንባብ ተማሩ፡፡ ቀጥሎም የቤተክርስቲያን ትምህርት ተከታተሉ፡፡ ከዚያም ወደ ዳንግላ ሄደው ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ ተብሎ ይጠራ በነበረ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማሩ። ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡
አቤ ጉበኛ በመጀመሪያ ሥራ የጀመሩት ማስታወቂያ ማኒስቴር ቀጥሎ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሲሆን በመንግሥት ሥራ ከስድስት ዓመት የበለጠ አልቆዩም፡፡ ሕይወታቸውን በአብዛኛው የገፉት በደራሲነት ነው፡፡ አቤ ጉበኛ ለትውልድ ቅርስ የሚሆኑ የተለያዩ ድርሰቶችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ በመድረስ አባትመዋል፡፡ ካሳተሟቸው በርካታ መጽሐፎች በተጨማሪ “ቂመኛው ባሕታዊ” እና የ “ደካሞች ወጥመድ” የተባሉ ቲያትሮች አዘጋጅተው ለሕዝብ ታይተዋል፡፡
በአቤ ጉበኛ ብዕር ተከሽኖ የቀረበና በ፲፱፷፮ ዓ.ም. ዳግም ለኀትመት የበቃው እና አብዮቱ በሀገሪቱ ሲቀጣጠል በኀብረተሰቡ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ የተነበበው “አልወለድም” የተሰኘው መጽሐፍ ማንም ሰው ከእናቱ ማሕጸን ጀምሮ ምኞትና ጥንቃቄ ሊለየው እንደማይገባ የሚያትት ሲሆን በመታየት ላይ ያለው እውነታ ግን አዳጋች የሆነና የሰው ዘር በድህነት ተወልዶ አድጎና ኑሮው በድህነት እንደሚያልፍ ያሳያል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ አግባብ አለመሆኑንም ይቃወማል፡፡
መጽሐፉ የሰው ልጅ የሚደርስበትን መከራ በመቃወም ይሞግታል፡፡ የሰው ልጅ መብት በአግባቡ መጠበቅ እንዳለበትም ያስረዳል፡፡
ምንጭ: የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ። |