አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ በ1860 ዓ.ም ጎንደር ዘጌ በተሰኘችው ስፍራ ተወለዱ፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው የሚነገርላቸው አፈወርቅ በልጅነት ዕድሜያቸው አዲስ አበባ መጥተው አደጉ።
ለዘመናዊት ኢትዮዽያ ሥልጣኔ መስራች የሆኑት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ያውሮፓን ሥልጣኔ ቀስመው እንዲመጡ ወደውጭ ሀገር ከላኳቸው ብልህ ወጣቶች መካከል አንዱ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ ናቸው።
አፈወርቅ የ20 ዓመት ብላቴና ሳሉ በአጤ ምኒልክ በጎ ፈቃድ ከሁለት ወጣቶች ልጅ ጉግሳ ዳርጌ እና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል ጋር በ1880 ዓ.ም ወደ ስዊዘርላንድ ተላኩ። ከዚያ ከደረሱ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸውና ባልታወቀ ምክንያት ወደ ጣሊያን ቱሪን ሄደው በኮሌጅ ኢንተርናሲዮናል ደ.ቤሊ አርቲ ከፍተኛ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ተከታተሉ። ከአድዋ ጦርነት በ1986 በፊት ወደ ኢትዮዽያ ተመልሰው በ1882 በቤተመንግስት ባለሟልነትና በሠዓሊነት ሙያ ያገለገሉት አፈወርቅ፥ በተለይ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በመቀያየማቸው በ1888 ዓ.ም. በስደት መንፈስ ወደ ኢጣሊያ ተመለሱ። በናፖሊ የምስራቅ ጥናት ኢንስቲቲዩት የአማርኛ ቋንቋ በማስተማር የፕሮፌሰርነት ማእረግ አግኝተዋል።
አፈወርቅ በኢጣሊያ ሳሉ ለኢትዮዽያ ዘመናዊ ሥነ ጽሁፍ ዕድገት የበኩር ልጅ ሊያሰኙዋቸው የቻሉትን የአማርኛ መጻሕፍት የጻፉ ሲሆን እንደገና ወደሀገራቸው በ1922 ዓ.ም. እስከተመለሱ ድረስ፥ በግእዝ፥ በአማርኛ፥ በኢጣሊያንኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የመማሪያ መጻሕፍት፥ የታሪክ እና የፈጠራ ልቦለድ መጻሕፍትን አሳትመዋል።
አፈወርቅ በ1902 ዓ.ም. ሮማ ባሳተሙት ዳግማዊ ምኒሊክ በሚለው የታሪክ መጽሐፋቸው ከግዕዝ ጽሑፍ ባህል ወደ ዘመናዊ አማርኛ ኪናዊ ሥነጽሑፍ ለተደረገው ሽግግር በተለይ በ1908 ዓ.ም. በሮም ባሳተሟት ጦቢያ-ልቦለድ ታሪክ የፈጠራ ሥራቸው-በኢትዮዽያ የአማርኛ ዘመናዊ ሥነጽሑፍ መሥራች ካሰኛቸው ማእረግ ባሻገር በአፍሪካ ቋንቋዎችም ታሪክ- በሀገርኛ ቋንቋ በመጻፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የሚል ምስክርነት አግኝተዋል።
ቀደም ሲል ለሀገራቸው በአስተርጓሚነት፥ በጉምሩክ ሥራ ኃላፊነት ነጋድራስነት እና በአምባሳደርነት ሮም ያገለገሉት አፈወርቅ በኢትዮዽያና ኢጣሊያን ጦርነት ወቅት 1924 - 1933 ኢጣሊያን ወገን ሆነው በ የቄሣር መንግስት መልእክተኛነት በሀገራቸው ልዩ በደል ፈጽመዋል በሚል ከነፃነት በኋላ በ1933 የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው በጅማ ጅሬን እሥር ቤት ለ6 ዓመታት በግዞት ቆይተው፥ በእርጅና እና በጤና ማጣት መስከረም 15 ቀን 1939 ዓ.ም በ79 ዓመታቸው አረፉ።
ምንጭ:ብርሀነመስቀል ደጀኔ 2000ዓ.ም ብራና.ማ.ቤ ካሌንደር። |