"ደማሙ ብእረኛ "
መንግስቱ ለማ ቀደምት የኢትዮዽያ ሊቃውንት ከነበሩት ከአለቃ ለማ ኃይሉ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አልማዝ ይልማ ሰኔ 1 ቀን 1916 ዓ.ም ሐረር አደሬ ጢቆ በተባለ አካባቢ ተወለዱ።
መንግስቱ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው በሊቁ አባታቸው እና በወቅቱ መምህራን ባህላዊውን የቤተ ክህነት ትምህርት ከዜማ እስከ ጾመ ድጓ እና የግዕዝ ቅኔን ጠንቅቀው "የልጅ ሊቅ" ተባሉ።
በኢጣሊያ ወረራ ወቅት 1929 -1933 በጣሊያን አገዛዝ ሥርዓት ትምህርት በ"ፓጃላ" ሦስት ዓመት፥ ከነፃነት በኋላም በአንድ ዓመት ተኩል እድሜ ውሰጥ 1934 - 1935 በሚሲዮናዊው ሙሴ እንቶን ጆነስ ትቤት እስከ አራተኛ ክፍል ዘመናዊውን ትምህርት አጠናቀዋል።
መንግስቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል በ1936 ዓ.ም. አዲስ አበባ መጡ። እስከ 1939 ዓ.ም. በኮተቤ ቀ.ኃ. ሥላሴ ት/ቤት ተከታተሉ።
በ1940 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በማግኘት ወደ እንግሊዝ ሀገር የሄዱት መንግስቱ፥ በለንደን ለአንድ ዓመት በ"ሬጀንት ስትሪት ፓሊቴክኒክ ኮሌጅ"፥ ቀጥሎም በእውቁ "ለንደን ስኩል ኦፍ ኤኮኖሚክስ" የሥነምጣኔ ትምህርታቸውን ተከታተትለዋል። መንግስቱ ምንም እንኳን ኋላ ጥናታቸውን ሳያጠናቅቁ በ1946 ዓ.ም. ወደ ሀገራቸው ቢመለሱም፥ በለንደን ቆይታቸው በ1941 ዓ.ም "በብሪታኒያ የኢትዮዽያ ተማሪዎች ማህበረሰብ"ን የመሰረቱ ንቁ የለውጥ መሪ ነበሩ፥ ማህበሩን በዋና ፀሐፊነት እና በፕሬዚዳንትነት የመሩ።
የሐዲስ ሐሳብና የለውጥ ልሳን የነበረውን የማህበሩን መጽሔት "እጓለ አንበሳ" LION CUB በመመሥረት ወጣት ኢትዮዽያውያን ምሁራን የለውጥ ሐዋርያዊ ተልእኮአቸውን በምን መልኩ መወጣት እንዳለባቸው በገናን ብእራቸው The best system of Ideas ድምፃቸውን ያሰሙ ፍቁረ ኢትዮዽያ ከነበሩት እውቅ እንግሊዛዊቷ ኢትዮዽያዊት ሲልቪያ ፓንክረስትን ከልጃቸው ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወዳጅነት የመሰረቱ፥ ይበልጡን ጊዜያቸውንም ታላላቆቹ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ፈላስፎች ሥራዎች እና የቴአትር ድርሰት "በሰሎች"ን የእነበርናንድ ሾው፥ ኢብሰንን። ስትራገድበርግን፥ ጋል ስዌርቷን ወዘተ... የመሳሰሉ ፀሐፊ ተውኔት ሥራዎች በስፋትና በጥልቀት ያነበቡ፥ የተመራመሩ ነበሩ።
ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሲቪል አቪዬሽን 1940 -1950 በኃላፊነት፥ በሕንድ የኢትዮዽያ አምባሳደርነት 1950 -1955 እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በምርምር ማእከል ኃላፊነት 1955 -1962 ያገለገሉት መንግስቱ፥ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ በተቋቋመው የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር "የብሔራዊ ቋንቋ መርሐ ልሣን" መሥራች እና ዋና ፀሐፊ 1962 -1967 ፥ የ"ብሔራዊ ቋንቋ አካዳሚ " ዋና ፀሐፊ 1967 -1971 በመሆን፥ ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለት ሞታቸው በአ.አ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር መምህርነት በማገልገል በአጠቃላይ - በኢትዮዽያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ እድገት በአማርኛ ሥነ ግጥም ቅኔ እና በቴአትር ድርሰት "ተዋነይ"ነት በተመራማሪነት እና በመምህርነት ----- ግምባር ቀደም ሆነው ----- በነበሩ ኢትዮዽያዊ ባህልና በ"ውጪው"ዓለም አዳዲስ ሐሳብ "ተዋህዶ" ሥርዓት የኢትዮዽያን የሥነ ፅሑፍ ህዋ በብዕር ቀለም አድምቀውታል፤ አዳዲስ የቴአትር ጥበባት ባለሙያዎች አፍርተዋል።
መንግስቱ ለማ "የግጥም ጉባኤ" 1950፥ "ያባቶች ጨዋታ" 1953፥ "ባሻ አሸብር ባሜሪካ 1967" በተሰኙት የሥነ ግጥም ሥራዎቻቸው ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ አዳዲስ የግጥም ስልትና ዘይቤ የመሰረቱ፥ "ያላቻ ጋብቻ" 1956 እና "ጠልፎ በኪሴ" 1961 በተሰኙት ተውኔቶቻቸው ደግሞ "ለኢትዮዽያ ኮሜዲ ቴአትር በር ከፋች" "ኮሜዲያችን ዘመናዊ መልክ እንዲጎናፀፍ ያደረጉ የመጀመሪያው ኢትዮዽያዊ" የሚል ልዩ አክብሮት ያገኙ የሥነ ፅሑፍ ሰው ናቸው።
በኢትዮዽያ ሥነ ጥበባት አምባ "ደማሙ ብዕረኛ" የሚል ልዩ ስያሜ ስላገኙት እኚህ የዕደ ጥበብ ባለሙያ፥ ሠዓሊ፥ ባለቅኔ፥ ፀሐፌ ተውኔት መምህር እና ተመራማሪ የቀለም ሰው ቶማስ ኬን፥ ኡላን ዶርፍ፥ ሬዱልፍ ሞልቫር፥ ሪቻርድ ፓንክረስትና ወዘተ...የመሳሰሉ እውቅ የውጪ ፀሐፍት ታሪካቸውን በአድናቆት የዘከሩ ሲሆን፥ ዛሬም ድረስ እየተዘከሩ ነው።
በጠቅላላ መንፈሳቸው "የጥንታዊቷና የአዲሲቱ ኢትዮዽያ መገናኛ አንድ ድልድይ" እንደነበሩ የተመሰከረላቸው፥ በ1961 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የስነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ፥ በ1962 ዓ.ም ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ተሸላሚ የነበሩት መንግስቱ ለማ ሐምሌ 21 ቀን 1980 ዓ.ም. አረፉ። |