ባለታሪኩ ከበደ ሚካኤል ጥቅምት 23 ቀን 1909 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ -- ደብረ ብርሃን ከተማ አካባቢ ገርም ገብርኤል አጥቢያ ተወለዱ።
በህፃንነታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ልዩ ታሪኮች በወግ መልክ በመተረክ እንደ አነፅዋቸው የመሰከሩላቸው እናታቸው ወ/ሮ አፀደ ሚካኤል ጀንዲ እስከ ዘጠነኛ አመታቸው ድረስ በባህላዊን የግዕዝ ትምህርት እንዲቀስሙ እንዳስቻሏቸው ይነገራል። ከበደ በ1918 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥተው በእናታቸው ወንድም በአቶ ሰይፉ ሚካኤል ልዩ ድጋፍ በ"አሊያንስ ፍራንሴስ" በፈረንሣይኛ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፥ በላዛሪስ ሚሲዮንም የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
ከበደ ሚካኤል እስከ ጣሊያን ወረራ ዋዜማ ድረስ በነበረው የተማሪነት እና የወጣትነት ቆይታቸው ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር በትርፍ ጊዜያቸው ልዩ ልዩ የፈረንሳይኛ መጸሐፍትን በማንበብ የቋንቋ የንግግር ችሎታቸውን አዳብረዋል። አንድም - በዘመናቸው ከነበሩት ቀደምት ታዋቂ ኢትዮዽያውያን ምሁራን - የአለቃ አፅመ ጊዮርጊስን፥ የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን፥ የፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/ኢየሱስን፥ የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን እና የነቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴን አዳዲስ ሓሳቦች ቀስመዋል። ከትምህርት ቤት መምህራኖቻቸው ይሰጡዋቸው በነበረ ልዩ ድጋፎችም የግሪክን የሮማውያንን፥ የእንግሊዝን፥ የፈረንሳይን፥ የጀርመንን፥ የሩሲያን እና የኢታሊያን ፈላስፎች ጠቢባንና ሳይንቲስቶች "ታላላቅ ሰዎች" መጻህፍት አንብበዋል መርምረዋል።
ከኢጣሊያ ወረራ 1929 -1933 ዓ.ም በኋላ በ"ነፃነት መዝሙር" -የቅኔ መንገድ ልዩ ተሰጥኦዋቸውን አሀዱ ያሉት ከበደ ሚካኤል ከሃገራችን ደራሲያን በላቀ መልኩ በዘመናዊ እሳቤና ሥነ ጽሑፋዊ ተሳትፎአቸው ከ16 በላይ የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎች ፍልስፍና፥ ሥነመለኮት፥ ሥነ ትምህርት፥ ሥነምግባር፥ ሳይንስ፥ ሥነ ጥበባት፥ ቅኔ፥ ተውኔት "ብርሀነ ህሊና" በብእሮቻቸው መግለጫነት በአማርኛ፥ በፈረንሳይኛ፥ በእንግሊዝኛ፥ እና በጣሊያንኛ ቋንቋዎች ከ90 በላይ በታተሙ ከ200 በላይ ባልታተሙ ወጥና ትርጉም ድርሰቶቻቸው የኢትዮዽያን ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ አድማስ አስፍተዋል።
በአዳዲስ ሀሳቦች "አብራሄ ህሊና"ነት ሀዲስ ትውልድ ያፈሩት ፈላስማውና ባለቅኔው ከበደ ሚካኤል፥ ዘመናዊ ኢትዮዽያን ለማደራጀት በተደረገው ተጋድሎም በልዩ ልዩ የሚኒስትርነት ማእረጎች በግምባር ቀደምነት አገልግለዋል።
ፈላስፋ፥ ባለቅኔ፥ ፀሐፊ ተውኔት፥ ደራሲና አንጋፋው ጋዜጠኛ ከበደ ሚካኤል በአገራችን እንግዳና የመጀመሪያ የነበረውን የቀ.ኃ.ሥ. የ1957 ዓ.ም የሥነ ጽሑፍ ሽልማት በቀዳሚነት የተቀበሉ የ"ቀለም ሰው" ሲሆኑ፥ በዘላቂነት ሐዲስ ትውልድ ላፈራው የላቀ አስተዋፀኦዋቸውም የአ.አ.ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 26 ቀን 1990 ዓ.ም በሥነ ጽሑፍ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል።
ክቡር ደ/ር ከበደ ሚካኤል ኅዳር 3 ቀን 1991 ዓ.ም በ82 ዓመታቸው አረፉ። "ሰኔ 21 ቀን የከበደ ሚካኤል መታሰቢያ ቀን" ሆኖ ተሰይሟል።
ምንጭ:ብርሀነመስቀል ደጀኔ 2000ዓ.ም ብራና.ማ.ቤ ካሌንደር። |