<b>የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት</b> ዘውዴ ረታ 2004 ዓ.ም

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ዘውዴ ረታ 2004 ዓ.ም

  


ሐምሌ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ለተከበረው ለ120ኛ ልደታቸው መታሰቢያ ላይ  ዘውዴ ረታ በጻፉት  "የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት" መጽሐፍ ዙሪያ በያሬድ ጥበቡ የቀረበ   የመጽሐፉ ቅኝት።

ከወራት በፊት “የሁለት አምባዎች ወግ” የሚል የሁለት መጽሃፎች ግምገማ ጀምሬ፣ ወግ አንድን በአቶ በረከት ስሞኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ላይ ተችቼ፣ ሁለተኛው ወግ ስለ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መጽሃፍ ይሆናል ብዬ ቃል ገብቼ ነበር ። ሆኖም የኮሎኔሉን መጽሃፍ ለመተቸት ምሬቴ ያልበረደ ሆኖ ስለተሰማኝ ዝምታን መረጥኩ ። ክፍል ሁለትን ስትጠባበቁ ለነበራችሁ የ”ፍትሕ” ታዳሚዎቼ ማካካሻ እንዲሆንልኝ እነሆ የአምባሳደር ዘውዴን ታላቅ ሥራ አንብቤ፣ ለመገምገም እንኳ ስልጠናውም ሆነ አቅሙ ባይኖረኝም፣ ከመጽሃፉ የተማርኩትን ባካፍላችሁ ይጠቅማል ብዬ 809 ገጾች በማንበብ የደከምኩበትን መጣጥፍ እነሆ!


ክፍል አንድ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንግስ በአል ተጀምሮ ለ100 ገጾች እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ አምስቱን አመታት እያላጋን ይዞን ይዘልቃል ። በዚህ ክፍል እጅግ ቀልቤን የሳበው፣ ንጉሠ ነገስቱ “በመልካም ፈቃዳቸው” በሕገ መንግስት የምትተዳደር ሃገር ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸው ነው ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተራማጅነት ጎልቶ የሚወጣበት ዘመን ነው ። ቀኃሥ የ39 አመት ጎልማሳ ቢሆኑም በልጅነታቸው የቆነጠጣቸው የካቶሊክ ቄስ ምን ያህል አስተምህሮው ሰርጾ እንደገባባቸው መረዳት ይቻላል ። አባ እንድርያስ ዣሮሶ አንጎል የሚያዞሩ ምሁር መሆናቸው የሚገባን 300 ገጾችን ጠብቀን፣ በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ ሲሟገቱ ስናገኛቸው ነው ። በአውሮፓ አስተሳሰብ ተፈሪ መኮንንን አንፀዋቸዋል›› ባይ ነኝ። ያለበለዚያማ ገና ዘውድ በጫኑ በዘጠኝ ወራቸው፣ ህዝቡ ሳይጠይቅ ሕገ መንግሥት ማስረቀቅን ምን አመጣው?

የአውሮፓን የዘመናዊነት ጭራ ለመያዝ ሩጫውን የጀመሩት ንጉሠ ነገስቱ ራሳቸው እንደነበሩ ስንገነዘብና፣ ለዚህም ግፊቱን የሚያደርገው የኢትዮጵያ አፈር የሕዝቡ ጥያቄ ሳይሆን፣ በዘመናዊነት ስም የመጣው የአውሮፓ ትምህርት መሆኑን ስንረዳ፣ ሃገሪቷ ወደፊት ከመራመድ ይልቅ ለምን ባለችበት እንደምትረግጥ ፍንጭ ይሰጠናል ። የ120ኛ የልደት በአላቸውን የምናስብላቸው፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሕይወት የሚያስተምረን ነገር ቢኖር ሃገርን ያህል ነገር በጥቂቶች ሃገር ለማዘመን በቆረጡ ጀግኖችና ምሁራን፣ አንዴ ከምዕራብ አንዴ ከምስራቅ ርዕዮተ ዓለምና የፈጣን ልማት ስትራቴጂዎች እየተበደሩ፣ ከመፈክር መፈክር እየተንከባለሉ፣ ሕዝቡን ከዳር ተመልካች አድርጎ፣ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ነው። ይህ ዛሬም ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ መሆኑን ነው ከአምባሳደር ዘውዴ ታላቅ ሥራ የተማርኩት ።

ይህንኑ የ1923 ሕገ መንግስት እንዲያረቅ የተቋቋመው ኮሚቴ አባል በነበሩት በኮሚቴው ሰብሳቢ በልዑል ራስ ካሣ ሀይሉ ና በበጅሮንድ ተክለ ሃዋርያት መካከል የሚጦፈውን ክርክር ለማዳመጥ፣ አምባሳደር ዘውዴ አዳራሹ ድረስ ይዘውን በመግባት መከዳዎቹ ላይ አስቀምጠው ያስኮምኩሙናል ። ያውም በእረፍት ጊዜ ከቤተ መንግስት ከተላከው ብርዝና ጠጅ እያስጎነጩን ። ራስ ካሣ “ከኢትዮጵያዊ ልማዳችን ወጥተን በሕገ መንግስት መተዳደር ለምን አስፈለገ?” ለሚለው ጥያቄያችው የሚሰጣችው መልስ “የፈረንጆቹን ሥልጣኔ ካልተከተልን ይወሩናል” የሚል ስለነበር፣ “ፈረንጆች የሚወሩን የነርሱን ልማድ ስላልተከተልን ሳይሆን፣ ሀብታችንን በመፈለግ ነው” የሚለው ድምጻቸው ሲያስገመግም በመገረም አዳመጥኳችው ።

ስለኚህ መስፍን ሌላው የገረመኝ ጉዳይ፣ በጅሮንድ ተክለሃዋርያት ከተማሪው ንቅናቄ መሪዎች ባልተናነሰ ቋንቋ “ዛሬ ባለንበት አለም ላይ ፣ ክቡራን መሳፍንት የምታምኑበት የአገዛዝ ደንብ በሙሉ ተለውጧል ። የአገር አስተዳደር ሥልጣን እንደግል ንብረት ለዘር የሚተላለፍ መሆኑ ጭራሽ ከተወገደ ዘመን የለውም” እያሉ ሲሞግቷቸው፣ ራስ ካሣ ሲመልሱ “በእኛና በምናስተዳድረው ሕዝብ መካከል ያለውን ፍቅርና መተማመን አናውቅም ብላችሁ እኛን ለሕዝብ የማናስብ ክፉ ገዢዎች አድርጋችሁ የምትቆጥሩን ከሆነ፣ በአንድ ገበታ ላይ ተሰብስበን ለትልቁ የአገር ጉዳይ አብረን መሥራት የለብንም “ ብለው ሲመልሱ፣ ይሄ እስከዛሬም ሰቅዞ የያዘንን ደዌ - በአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መሃል እንደ ወዳጅና ጠላት የጎሪጥ የምንተያይበት ክፉ በሽታ - የሚያስከትለው ጦስ፣ በጥራት ይታያችው እንደነበር ስገነዘብ ባግራሞት ተዋጥኩ ።

ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን ገና መጽሃፉ ሲጀመር ገጽ 28 ላይ፣ ገና በማለዳ በ1923 ዓም የሰማነው ሆኖ ሳለ፣ ከ25 አመታት በሁዋላም፣ ጸሃፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስን ከስልጣን ለማውረድ በእቴጌ ቪላ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴና አቶ መኮንን ሀብተወልድ ጋር የህቡዕ/ምስጢራዊ ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅትም ራስ ካሣ ይህንኑ ፍራቻችውን ከመሰንዘር አልቦዘኑም ። ሁለቱ ከድሃ ወገን የተገኙ ታላላቅ ባለሥልጣኖች ጸሃፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ መኮንን ሀብተወልድ ቀደም ብሎም “የገጠሩን ሕዝብ ከመንግስት ጋር ለማቀራረብ” በሚል፣ አገረ ገዢዎቹን ሳያማክሩ 25 ምስለኔዎችና 25 ጭቃ ሹሞችን አዲስ አበባ አስመጥተው በማሰልጠናቸው ያዘኑት መስፍን ፣ ለአቶ መኮንን ሀብተወልድ ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ “ሕዝቡ...የፈረንጅ ፊደል የቆጠረ ሁሉ፣ ከየሜዳው ተነስቶ ልግዛህ ቢለው አይቀበልም ። አንድ ሰው የሕዝብ ገዥ እንዲሆን ከንጉሥ ተመርጦ የሚሾመው፣ ከድሃ ወገን የተወለደው ብቻ ነው የሚል ደንብ የለም ... በዚያ የመከራው ስደት ዘመን፣ እጅግ ሠለጠነ በተባለው በእንግሊዝ አገር እንዳየነው፣ ጌታም በጌትነቱ፣ ድሃም በድህነቱ በሰላም ሠርቶ የሚኖር ነው ። መንግስት የሚያስበው ለሁሉም ወገን እኩል ዳኝነት እንዲኖር ዋስትና መስጠትን እንጂ፣ በትውልዱ ምክንያት አንዱን ካንዱ በሥልጣን በማበላለጥ አይደለም...በአገራችን ግን እናንተ የምትጠሉት መሳፍንትና መኳንንት፣ ከዚህ ቀደም ለአገር ነፃነት መስዋዕት እየሆነ ብዙ የሚያኮራ ታሪክ የፈፀመና የአገርን ትልቅነት አስከብሮ የኖረ መሆኑን መርሳት አይገባም” ይሉናል ። መስፍናዊ ድምፃቸው ዛሬም ያስገመግማል ።

በስደት ሕይወታችን መጠለያና ብሎም እንደ የጥረታችንና ዕድላችን ትምህርትና ሃብት የሰጡን የምዕራብ ሃገራት የሚመሩበት መሠረታዊ ፍልስፍና ይኼው የራስ ካሣ ፍልስፍና በመሆኑ፣ በመደብ ትግል ስም ያተራመስናትን ሃገራችንን ስናስብ ሀዘን ሊሰማን ይገባል እላለሁ። ይበልጥም ግን ያሳዘነኝ ለውጥ ፈላጊ የነበረው የኔው ትውልድ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥር ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙት ጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ መኮንን ሀብተወልድ የህልሙ ተካፋይ መሆናቸውን ሳይረዳ መጨካከን ላይ ልንዳረስ መቻላችን ነው። የመጽሃፉ አካልም ባይሆን፣ የመኮንን ሀብተወልድ ዕጣ እንደርሳቸው ለውጥ በሚፈልጉ፣ ነገር ግን ትዕግስቱ ባልነበራቸው ጄኔራሎች ጥይት መገደል በጄኔራል መንግስቱ ነዋይ መንግስት ግልበጣ ሙከራ መሆኑን ስንረዳም፣ ይሄ እስከዛሬም ሥልጣን ላይ ያሉ ዜጎቻችንን በሃገር ጠላትነት የምናይበት አተያይ፣ ይዞን እንጦርጦስ ከመውረዱ በፊት እጅግ ልናስብበት የሚገባ ይመስለኛል ። እያንዳንዱ ባለሥልጣን መመዘን ያለበት በወሰነው ውሳኔ፣ ይዞ በተከራከረው አቋም እንጂ ለኢትዮጵያ መንግስት በማገልገሉ እንደ ጠላት መቆጠር የለበትም ባይ ነኝ ። ሃገሪቱ ያለመንግስት መኖር ስለማይቻላት ነው ይህን ማለቴ ።

በተቃራኒው ግን ከልዑል ራስ ካሣ መማር እንችላለን ። በሕገ መንግሥት አርቃቂው ኮሚቴ ውስጥ የጦፈ ልዩነት የነበረ ቢሆንም፣ የልዩነት ነጥቦቹ ከጽህፈት ሚኒስቴር በመጡ ቃል ተቀባዮች ሰፍሮ ለንጉሰ ነገስቱ እንዲተላለፍ ሊቀ መንበሩ ራስ ካሣ ስብሰባውን ሲያሳርጉ “ሁላችንም ከልባችን የሚቻለንን ማድረጋችንና መድከማችን የሚካድ አይደለም ። በስብሰባችን ላይ ስንነጋገር፣ አለመስማማትና አለመጣጣም ደርሶብናል። ይህ መቼም የአገር ጉዳይ የሆነ ሥራ ሲሠራ የሚያስከትለው ችግር ነው። በዚህም የተነሳ በአንዳንድ ጉዳይ በሐሳብ መከፋፈላችን ለጊዜው በመካከላችን ቅሬታ ያሳደረ መስሎ ቢታይም፣ ወዳጅና ጠላት አድርጎ የሚለያየን መሆን የለበትም። ይህን ሳንስማማ የቀረንበትን ነገር ንጉሠ ነገሥቱ መርምረው ውሳኔ በሚሰጡበት ዕለት፣ ጉዳያችን ይዘጋል” ይሉናል። ለኔ ትውልድ እጅግ ባዕድ በሆነ ሆደ ሰፊነት ያነጋግሩናል። የኔ ትውልድና የቀድሞዎቹ ታላላቆች ሳንተዋወቅ ተጨካክነናል። ሆኖም ባለፉት ሃያ አመታት፣ ዕድሜ ለአምባሳደር ዘውዴ ረታና መሰሎቻቸው፣ ከራሳችን ታላላቆች አንደበት እንድንማር ያደረጉት ድካም ፍሬ እያፈራ ነው። ከአዲሱ ትውልድ ድንቅዬዎች መካከል፣ የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ወጣት ተመስገን ደሳለኝ፣ የ”ነፃነት ለኢትዮጵያ” ሬዲዮ ጋዜጠኛና ባለቅኔ ኢሳይያስ ልሳኑ፣ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁንና፣ በደራሲና ባለቅኔ በዕውቀቱ ሥዩም ጥልቅ ሥራዎች ውስጥ የተስፋ ብርሃን እያጮለቅን ነው ።

ወደመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ስንመለስ፣ በአርቃቂ ኮሚቴው ውስጥ የተፈጠረው የልዩነት ሃሳብ ለጃንሆይ በቀረበላቸው ጊዜ የተናገሩትን ስናዳምጥ፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዴሞክራሲን በሚመለከት የነበራቸው አስተሳሰብ እንዲሁ ከዘመኑ የቀደመ ምናልባትም ሥርነቀል ሊባል የሚችል እንደነበር እንገነዘባለን። እንዲህ ይላሉ ፣ “የሠለጠኑት አገሮች የሕገ መንግስታቸውን አመሠራረት የተመለከትን እንደሆነ፣ መንግስትን ለማቆም፣ መንግሥትን ለመሻር የመንግሥትን ሥራ ለመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን ያለው ፓርላማው ሆኖ እናገኘዋለን። እኛ በዚህ ደረጃ ለመድረስ የብዙ ዘመናት ድካም የሚጠይቀን ቢሆንም፣ ቅድም በጅሮንድ ተክለሃዋርያት እንዳስረዳው፣ አጀማመራችን የዴሞክራሲን መንገድ የሚከተል ሆኖ እንዲታይ፣ በመወሰኛና በመምሪያ አማካሪዎቻችን መካከል የመደመጥም ሆነ የወንበር ልዩነት እንዳይደረግ መጠንቀቅ አለብን” ይላሉ። እኔን የተሰማኝ፣ ገና በማለዳ፣ የዛሬ 80 አመት፣ እንዲህ አይነት የዴሞክራሲ ጥብቅና የነበራቸው መሪ፣ ከ43 አመታት በሁዋላ በየካቲት 66ቱ አብዮት ሲዋከቡ፣ “የድካማችን ውጤት ነው” የሚል ውስጣዊ እርካታ ተሰምቷቸው እንደሆንስ ብዬ እንድጠራጠር ከንክኖኛል። በኔ ዕምነት መሪዎችን መሪ የሚያደርጋቸው ከተራው ዜጋ የማይጋሩት አንድ ልዩ ባህሪ ስላላቸው ይመስለኛል። አለበለዚያ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለአልጋቸው ተኪ ሳያዘጋጁ ማርጀትን ለምን መረጡ? አንድ ሁላችን የምንስማማበት ፋይዳ ቢኖር፣ በየካቲት 66 ከታች፣ ከሕዝብ የተነሳውን ተቃውሞ በአመጽ ለመደምሰስ ፍፁም ፈቃደኛ ያልነበሩ መሆናቸውን ነው። የካቲትም ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ለአመታት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ግፊት ያደርግ ለነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የነበራቸው አባታዊ ስሜትንም፣ “ምናልባት ፊውዳላዊ ቅሪቱን ለማጥፋትና የገባሩን ነፃነት ለማምጣት የሚረዳ አጋዥ ሐይል” አድርገው አይተውት እንደሆንስ? ብዬ ርቄ እንዳስብ ገፋፍቶኛል። ከአንድ ደራሲ ደግሞ እንዲህ የማይገናኙ የሚመስሉ ክስተቶችን አያይዘን እንድናሰላስልና እንድናጠይቅ የረዳን ከሆነ ለስራው ትልቅነት ምስክር ይመስለኛል።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከተራማጆቹ ከነበጅሮንድ ተክለሃዋርያት ጋር በመወገን “የፌዎዳልሥርዓት በዓለም ላይ እጅግ የተወገዘና የተፋቀ ስለሆነ፣ለእኛ ለሥልጣኔያችን ጠቃሚያችን የሆነውን ሕገ መንግስት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስንመሰርት፣ ይኸው የተጠላው የፌዎዳል አሠራር ካልተጨመረበት ብለን ሳንስማማ ብንቀር ወዳጃችን በሆኑት በዓለም መንግስታት መሪዎች ዘንድ ምን ያህል ትዝብት እንደሚወሰድብንና፣ ጠላቶቻችንንም እንደምናስደስት ማወቅ አለብን” ሲሉም ጉዳዩን መዝጋታቸው የሚያሳየን ነገር ቢኖር፣ በዛሬው ዕለት 120ኛ የልደት በአላቸውን የምናከበርላችው የሃገር መሪ፣ ምን ያህል ከጊዜው እጅግ የቀደመ ሃገራዊ ርዕይ የነበራቸው ተራማጅ መሪ የነበሩ ቢሆንም፣ ራስ ካሣ “ተው አታስተምር!” ብለዋቸው ነበር በሚባሉ፣ የድሃ ልጆች በሆኑ ዝቅተኛ መኮንኖቻቸው እጅ ታፍነው መገደላቸው የሚሰቀጥጥ ታሪካዊ ፍጻሜ መሆኑን ነው ። በተለይ በወታደሮቻችው እጅ ለመገደል፣ ምክንያት ሆኖ የቀረበው “ካውሮፓ ወደኋላ አስቀሩን” የሚለው ክስ መሆኑን ስንረዳ፣ ታሪክ በምጸት የተሞላ መሆኑን ያስገነዝበናል ። ያውም በሳልከው ቢላዋ የመታረድ አይነት መሪር ምጸት ።

ከዚሁ እርስበርስ የመጨካከን ታሪክ ጋር በተዛመደ ሌላው ከአምባሳደር ዘውዴ መፅሃፍ የተማርኩት ጉዳይ፣ እኛ ዘወትር የምዕራቡን ጭራ ለመያዝ የምንቧችር ብንሆንም፣ እነርሱ ለጥረታችን ያላቸው ግምት በአመዛኙ አሉታዊ መሆኑን ነው ። ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መልካም ፈቃድ የቆመውን ሕገ መንግሥት፣ “ለአገሪቱ አመራር አስፈላጊውን ሥልጣን በሙሉ አጠቃልሎ የሰጠው ለንጉሠ ነገሥቱ ብቻ ስለሆነ፣ ዘመናዊውን የፓርላማ አሠራር ያልተከተለ ነው” በማለት ሲያጣጥሉት ታይተዋል ። ይህ እንግዲህ ከ80 አመታት በፊት ነው ። ምርጫ ያለን አይመስለኝም፣ ወደ ልዑል ራስ ካሣ የተቃውሞ ሃሳብ ነው የሚመልሰን ። ምዕራባውያን ዴሞክራሲን አስመልክቶ በሌሎች ሃገሮች ላይ የሚያደርጉት ትችት፣ ከሃገሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተዛምዶ የሚሰጥ ገንቢ ሃሳብ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን ማስጠበቂያ የአይዲዮሎጂ መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት መሆኑን ነው የምንገነዘበው። የሚገርመው ግን የምዕራባውያን ሃገራት ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር፣ ዴሞክራሲ ከላይ ወደታች የተሰጠ ህብስተ መና ሳይሆን፣ ሕዝቦች አስርተ አመታትን ታግለው በተራዘመ ሠላማዊና ሕጋዊ ትግል የተቀዳጁት መብት መሆኑን ነው። በአሁኑ ሰአት ሃገራችን ኢትዮጵያ ሌላ የሽግግር መድረክ ውስጥ ልትገባ የምትችልበት ንጋት ላይ ስለምትገኝ፣ ይህ ከራሳችንም ከምዕራባውያንም ታሪክ የምንማረው ትምህርት እጅግ ጠቃሚ ይመስለኛል። ከትርምስ የሚያድነንም ሊሆን ይችላል እላለሁ ።

እኒህ ታላቅ ደራሲ አምባሳደር ዘውዴ “ትምህርት የሥልጣኔ መሠረት” ባሰኙት በሶስተኛው ምዕራፍ፣ ተፈሪ መኮንን በአውሮፓ ጉብኝታቸው ወቅት ሰኔ 6 ቀን 1916 ዓ.ም የዛሬ 88 አመት ባረፉበት የሆቴል ክፍል ውስጥ ከልዑክ ቡድናቸው አባላት ጋር ስላደረጉት ጠቃሚ ውይይት ያካፍሉናል። ገና በወጣትነታቸው ጀምሮ ከረዳቶቻቸው ጋር እንዴት እንደሚመካከሩና ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ያስተምረናል። ባዶ እጃቸውን ከአውሮፓ ጉብኝታቸው ከተመለሱ በሁዋላ በግል ገንዘባቸው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን በሚያዚያ 1917 አም ሲያቋቁሙ ከቤተ ክህነትና ከመሳፍንቱ የደረሰባቸው ውግዘትና፣ ካለሙት ለመድረስ ተፈሪ መኮንን ያሳዩት ፅናት የሚደንቅ ነው። ሆኖም በእኔ አመለካከት፣ የመሳፍንቱና የቤተ-ክህነት ተቃውሞ፣ በቂ ተጽዕኖ መፍጠር ችሎ የአውሮፓን ትምህርት በምን መንገድ እንቀበለው በሚለው ላይ ሰፊ ክርክር አድርጎ የሃሳብ ሽግሽግ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ቢያመቻች ኖሮ የት በደረስን ነበር። መጥፎ ዕድል ሆኖ፣ ወደ ሃሜትና አሉባልታ የሚያሽቆለቁለው ባህላችን ተገቢውን ሽግግር እንዳናደርግ ዘግቶ ያሸናፊና ተሸናፊ ክፍፍልን ያስከተለ ሆኖ ተሰምቶኛል ። ምናልባትም ጃፓን በሄደችበት መንገድ ለመዘመን የነበረን ዕድል የተዘጋው ያኔ ይሆናል። ያኔ የጀመረ ሳናጠናና ሳንጨነቅበት ተሯሩጠን አቋም በመያዝ፣ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በሚል እልህ፣ እንደ ወዳጅ/ጠላት የምንተያይበት አስከፊ የፖለቲካ ባህልም እንደ ክፉ የጥርስ ህመም ይኼው እንደጠዘጠዘን ይኖራል ።

በተፈሪ መኮንን ተማሪነቴ ወቅት ለኔም ሆነ ለሃገሬ ጠቀሜታ ከሌለው ስለ እንግሊዝና ፈረንሳይ የ30 አመታት ጦርነት ታሪክ ከምማር፣ ምነው ትምህርት ቤቴን ለማቋቋም ስለተደረገው አበሳና ትግል በተማርኩ ኖሮ በሚል ቁጭት ነው ምዕራፉን ያጣጣምኩት። ጥቅምት 21 ቀን 1919 አም ለመጀመሪያ ጊዜ ለስኮላርሺፕ ትምህርት ወደ ውጪ የሚላኩት 33 ተማሪዎች አልጋ ወራሹ ተፈሪ መኮንን ፊት ሲቀርቡ ወጣቱ መስፍን ያደረጉላቸው የስንብት ቃል “...እኔ ሰው ነኝ፣ ሟች ነኝ። ለማትሞተው አገራችን ረዳት እንድትሆኗት እግዚአብሔርን እለምንላችኋለሁ...” የሚል ቢሆንም፣ ዛሬ ከ85 አመታት በኋላ፣ እንኳን ለሃገራችን ረዳት ልንሆናት ቀርቶ፣ መሬቷን ለመርገጥ እንኳ ከሕግ ውጪ በቂም በቀልና ክፋት የተከለከልን አያሌ መሆናቸንን ላየ፣ የተፈሪ መኮንንን ልመና ፈጣሪ የሰማው ለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር አያስችልም ።

ክፍል ሁለት - “ጥቁር ደመና በኢትዮጵያ ፀሐይ” የሚል ሲሆን ምናልባት ብዙዎቻችን የማናውቃቸውን ውሎች፣ ምስጢሮችና ሰነዶች ያካተተ ነው ። ሙሶሎኒ ሥልጣን ላይ ከመጣ በሁዋላ ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ጉባኤ አባል እንድትሆን መደገፉን፣ በወረራው ድሮ የአዲስ አበባ ውል መፈራረሙን፣ በመስከረም 1929አም የአምስት ሃገራት የጥናት ኮሚቴ ኦጋዴንን ጣሊያን እንዲያለማውና እንግሊዞች የዘይላ ወደብን ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት እንዲፈቅዱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲቀበሉት ሙሶሎኒ እምቢተኛ መሆኑና ንጉሠ ነገሥቱ የጦር ዝግጅት ከማድረግ በዲፕሎማሲ ላይ መተማመናቸውን የመሳሰሉ ቁምነገሮችን ያካተተ ነው። ሌላው ቀልቤን የሳበው የብሪታኒያው ተወካይ አንቶኒ ኤደንና የካናዳ አቻው፣ የሙሶሎኒ ወረራ በተጀመረ በ15ኛው ቀን፣ የነዳጅ ዘይት፣ ከሰልና ብረታ ብረት እገዳ እንዲደረግበት ለኮሚቴ 18 ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ ሙሶሎኒ እጅግ ከመንጰርጰሩ የተነሳ ትግራይንና ኦጋዴንን መውሰዱን ንጉሱ ከተቀበሉ፣ ወረራውን ሊያቆም ሃሳብ ወጥኖ የነበረ መሆኑን፣ ዘውዴ መረጃውን እየፈለፈሉ ያቀርቡልናል። ሆኖም አሜሪካና ጃፓን እኛ እናቀርብልሃለን ሲሉት የድርድር ሃሳቡን መተውንም ያካፍሉናል ። ከጁላይ 4 በአል ጋር በተያያዘ ኤን.ፒ.አር የሚባል የዲሲ ሬዲዮ ሲዘግብ እንደሰማሁት፣ አሜሪካ ሙሶሎኒን በምታደፋፍርበት ሰሞን፣ የአፍሪካዊ አሜሪካውያን መኖሪያ ቤቶች በእሳት እየጋዩ ነበር ። ምክንያት ሆኖ የተገኘውም ጥቁር የቤት አገልጋይ እመቤቱ መኝታ ቤት ቢላዋ ይዞ በመገኘቱ ነበር ። ማን ያውቃል ምናልባት የጥቁሯ ኢትዮጵያ ነፃነት መደምሰስ ለነጭ የበላይነት አስፈላጊ ነው ተብሎ ታምኖበት ሊሆን ይችላል ዋይት ሀውስ ያን ዓይነት አሳፋሪ ዝምድና ከሙሶሎኒ ጋር ለመጀመር የዳዳው ።

ደራሲው ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያላቸው አክብሮትና ፍቅር ጥልቅ በመሆኑ፣ ምናልባት የሚሸፋፍኑት ጉዳይ ይኖራል ብሎ ለተጠራጠረ አንባቢ እንኳ አይመቹም። ለምሳሌ በልጅ ኢያሱ አሟሟት ላይ “የዚህ መጽሃፍ ደራሲ... ኢያሱ አባ ጤና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በህመም ወይም በድንገተኛ አደጋ ሳይሆን በፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ያምንበታል” ገፅ 226 ይሉናል። ከኔ ትውልድ ሰዎች የኢጭአቱን፣ የኢሰፓውን፣ የመኢሶኑን፣ የኢህአፓውን፣ የህውሓቱን አመራር ወንጀሎች በምንደብቅበት ሰአት፣ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” ደራሲ ግን፣ የሚያከብሯቸውን ንጉሥ ድክመት ለመሸፈን አልዳዳቸውም። ይህ ራሱ ትልቅ ትምህርት ሆኖ አግኝቼዋለሁ ።
አምባሳደር ዘውዴ፣ ከነፃነት መመለስ በኋላ በእንግሊዞች አስገዳጅነት ጥር 23 ቀን 1934 አም ስለተፈረመው ውልና ስለተፈጠረው ሞግዚታዊ አስተዳደር፣ ከዚህ ጭቆና ለመላቀቅ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከመሳፍንቱ፣ ከአርበኞችና፣ ከወጣት ሚኒስትሮቻችው ጋር በመሆን እንዴት በትዕግስት እንደተወጡት ከዩናይትድ ስቴትስ አርካይቭ እስከ ለንደን ቤተ መዛግብት በመኳተን ተደብቆ የኖረውን ታሪክ ባፍ ባፋችን ያጎርሱናል። ወጣቱ ዲፕሎማት አክሊሉ ሀብተወልድ የማይናቅ አገልግሎታቸውን ሲጀምሩም እናያለን። ልጅ ይልማ ዴሬሳ በወቅቱ ሩዝቬልት ጋ ቀርበው በማስረዳት የአሜሪካውን መሪ ከኢትዮጵያ ጎን ለማሰለፍ በመቻላቸው የእንግሊዞችን የቅኝ ግዛት ህልም እንዴት እንዳከሸፉባቸው እንማራለን። በዚህ ክፍል አንድ ቀልቤን የሳበው ጉዳይ፣ ሁለተኛውን የአዲስ አበባ ውል ለመፈረም ከመጣው የብሪታኒያው ሎርድ ደላዋር ጋር ጃንሆይ ሲነጋገሩ “በእንግሊዞች ቤት ተቀጥረው የሚያገለግሉትም ሆኑ፣ እንግሊዞች በሚያዘወትሩት ሆቴሎችና ቡና ቤቶች የሚሠሩት ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸው የዘር ልዩነት በደል እጅግ የሚያሳዝን ነው” በማለት ለዘመናችን ገዢዎች በሚጠቅም አርአያነት ሲናገሩ እንሰማለን ። ዛሬ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊቶች የመካከለኛው ምሥራቅ የቤት ሠራተኞች በመሆን ለሚደርስባችው በደል፣ ሬሳ ከመላክ ውጪ፣ ኤምባሲዎቻችን የሚያሳዩትን ደንታ ቢስነት ላወዳደረ፣ ታላላቆቻችን ታላቅ፣ ልጆቻቸው ፍሬ ከርስኪ መሆናችንን ነው የሚያስረዳን ።

ዘውዴ የመንግሥቱ የውስጥ አሠራርና የውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ፣ የጽህፈት ሚኒስቴር መዛግብት ውስጥ ተደፍተው በማጥናት በቀላሉ የማይገኙ ጉርሻዎች ያቃምሱናል ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሚኒስትሮቻችው መሃል በቡድን አቋም የመያዝ ዝንባሌ ያዩ ሲመስላቸው “...ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ እንዳየነው፣ እኛ በምናደርገው ስብሰባ ላይ ይልማ ዴሬሳና አክሊሉ ሀብተወልድ እየተደጋገፋችሁ ታላላቆቻችሁ የሚያቀርቡትን ሓሳብ መቃወምና የራሳችሁን ትልቅ አስመስሎ መናገር፣ እንደ መልካም ሥራ አድርጋችሁ የምትቆጥሩት ይመስላል። እርግጥ ነው፣ አንድ ጉዳይ በጉባኤ ቀርቦ ሲጠና፣ እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ሓሳብ ሊኖረው ይችላል። ይህም የዘመኑ አሠራር የሚጠይቀው ነው ብለን እንቀበለዋለን። ነገር ግን፣ በየስብሰባው ላይ ሁለትና አንዳንድ ጊዜም ሦስት ሰዎች፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ሲደግፉም በአንድነት፣ ሲቃወሙም በአንድነት እየሆኑ የምናያቸው፣ ወደ ፓርቲ ያዘነበለ አሠራር ነው እንጂ፣ የዴሞክራሲን ወግ የተከተለ ነው ማለት አይቻልም” ይሉናል። መኮንን ባር፣ ኪሪያዚስና ጆሊ ባር ተቀምጠን ስናወግዛቸው የነበሩት ባለሥልጣናት እንዲህ አይነት ውይይት ያደርጉ ነበር ብለን እንኳ ለመገመት ጠርጥረንም የምናውቅ አይመስለኝም።

የኢትዮጵያን የጥንት ባህል አብጠርጥረው የሚያውቁት ልዑል ራስ ካሣ ሀይሉ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘንድ ያላቸው ተደማጭነት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሁለት ወሳኝ ወቅቶች ላይ ሃሳባቸውን ሲያስቀይሯቸው እናያለን። በመጀመሪያው፣ ከማይጨው ሽንፈት በኋላ ለጦሩ የማፈገፈግ ትዕዛዝ እንዲሰጡና ራሳቸውም ወደመናገሻቸው እንዲመለሱ ያስገደደ ሲሆን፣ ሁለተኛው፣ ስዊዝ ካናል ላይ ቸርችልን አልገናኝም ሲሉ እንዲያነጋግሩት የተገደዱበት ሁኔታ ነው። የዚህ ጠቀሜታው ግልፅ ሆኖ ታየኝና፣ ምን ታሰበኝ መሰላችሁ? መንግሥቱና መለስ ይህ ዕድል ያልገጠማቸው ሆኖ ተሰማኝ። ደግሞም፣ ለፕሬዝዳንትነት የሚታጨው ሰው፣ ነፃ አሳቢ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መገሰፅና ሃይ ማለት የሚችል፣ ለምሳሌ የፕሮፌሰር መስፍን ዓይነት ዜጋ ቢሆንስ ብዬ ከራሴ ጋር ተነጋገርኩ ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መኮንን እንዳልካቸው ይበልጥ ተሰሚነት የነበራቸው ለአመታት የንግድና እርሻ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተወልድ ከአድአ ቀሳውስት ቤተሰብ የተወለዱ የድሃ ወገን ቢሆኑም፣ አድራጊ ፈጣሪ ከመሆን እንዳላገዳቸው በክፍል ሰባት ውስጥ ለ140 ገጾች ታሪኩ ይተነተናል። የመኮንንን የለውጥና ጥገና ውጥኖችን ለተመለከተ፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ገጾች ውስጥ የራስ አበበ አረጋይን፣ የራስ ካሣንና ሌሎችንም ታላላቆች ክርክርና አስተያየት ላስተዋለ፣ የሃገራችን ትምህርትና አስተዳደግ ለአመራር ብቃት ያላቸው ሰዎች ለማፍራት አቅም እንደነበረው እንገነዘባለን ። ለምሳሌ አንድ የገረመኝ የመኮንን ሀብተወልድ ሪፎርም፣ በጣሊያን ጊዜ ሃገሪቱን ያጥለቀለቁትን የየመን ነጋዴዎች በአዋጅ ከማባረር፣ ጉራጌዎች ከሚኖሩባቸው ወረዳዎች ታታሪዎቹ ተመርጠው ከመንግሥት ለዘር የሚሆን ብድር ተሰጥቷቸው የንግድ ሱቆች እንዲከፍቱና በውድድር እንዲያሸንፏቸው በመደረጉ፣ አስቀድሞ “የአረብ ቤት” ይባሉ የነበሩ ሱቆች በእኔ ዕድሜ ወደ “ጉራጌ ሱቅ”ነት ሊቀየሩ ችለዋል ። ለመኮንን ሀብተወልድ ሃገር ወዳድነትና አርቆ አስተዋይነት ቀላል ምሳሌ ይመስለኛል ።

መኮንን ሦስቱን ወንድሞቻችውን የአውሮፓ ትምህርት ለማስተማር፣ ከዛሬ 93 አመት በፊት ጥር 24 ቀን 1911 አም ከእንጦጦ ራጉኤል የቆሎ ተማሪነት፣ ወደ አዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው ካመጧቸው በኋላ ይሰጧቸው ስለነበሩት ምክር፣ ደራሲው ከሦስቱ የሀብተወልድ ልጆች ጋር በመነጋገር ጨምቀው ያቀረቡልን “ምክር መስጫ” ፕሮግራም፤
1. “...ወደፊት ኢትዮጵያ የፈረንጆቹን ሥልጣኔ ለመቀበል የምትችለው፣ ከገባር ጭቆና አስተዳደርና ከመኳንንት ገዢነት ስትላቀቅ ነው
2. ...መኳንንትና የመኳንንት ወገኖች ዘመናዊውን ትምህርት አንማርም በማለታቸው፣ ለድሆች ልጆች ጥሩ ዕድል ከፍተዋል
3. ...የድሆች ልጆች ጠንክረው ከተማሩ፣ በዕውቀታቸው የአስተዳደሩን ሥልጣን ወስደው የኢትዮጵያን ሕይወት ማሻሻል ይችላሉ
4. ...ወደፊት የመኳንንት ወገን ሳይማር እንደዚሁ ከቀጠለ፣ የአባቱን ሀብት እንጂ፣ አባቱ ይዞት የነበረውን ሥልጣን አይወርስም
5. ... የአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን አመራር ብዙ ተስፋ የሚሰጥ ነው ። በዚህ አኳኋን ከቀጠለ፣ ኢትዮጵያ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመሻገር ዕድል አላት...”ገፅ 551 የሚሉ ነበሩ ።
እነዚህ ነጥቦች የዘመኑን ታላቅ ባለሥልጣን የመኮንን ሀብተወልድን ሃሳብ ጨምቀው የያዙ ናቸው ። በደራሲው ደግነት፣ ጥልቀት፣ ትጋት መደነቅ የግድ ነው ። ከባለሥልጣናቱ የግል ማህደርና የቤተሰብ ጨዋታ ሳይቀር ፍትፍት አድርገው በአፍ ባፋችን ያጎርሱናል ። እጅግ ከባድ ውለታ እንደዋሉልን ነው የሚሰማኝ ።
መጋቢት 18 ቀን 1939 አም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፣ በአቶ መኮንን ሀብተወልድና በጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ መካከል፣ የምእራቦችን ክስ ለማርገብና ሃገሪቱንም ለማዘመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንድ ምክር ይዘው እንዲመጡ በሰጧቸው መመሪያ መሠረት፣ በሦስቱ መሃል የተደረገው ውይይት፣ የሁለቱን ጓደኛሞች ሃገር የማዘመን ርዕይ ፍንትው ያደርጋል። መድረኩ የጭሰኛና ጉልተኛ ግንኙነትን እስከ መወሰን የሚደርሱ ሃሳቦች የቀረቡበት እንደነበር እናጤናለን ። ሆኖም ጸሀፌ ትዕዛዝ ደክመው ያቀረቡትን ረቂቅ ቢትወደድ እንዳልካቸው ከወሰዱት በሁዋላ የቀን ብርሃን ሳያይ እንደቀረ ታሪኩን የምንከታተለው በቁጭት ጭምር ነው ። ለቁጭትም መነሻ የሚሆነው፣ በ1953አ.ም ለተሞከረው መፈንቅለ መንግሥትም ሆነ፣ ኋላ ለተከተለው የየካቲት አብዮት፣ ወጣቱና ምሁሩ በሥርዓቱ ላይ አምርረው እንዲነሱ ትልቁን አስተዋጽዖ ያደረገው ትሁቱና ሩህሩሁ የኢትዮጵያ ገባር የሚገኝበት አስከፊ ሕይወት ነው ። ገባሩ፣ ታርዞ፣ ተርቦ፣ በቀላል ተላላፊ በሽታዎች አልቆ፣ በወባ ተቆልቶ የሚኖርበት ከባርነት ያልተሻለ ሕይወት የእኔ ትውልድ ሊቀበለው ያልቻለ የሕሊና ቁስል ሆኖበታል ። የጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ የለውጥ ሃሳብ የመሬት ሥሪት መሻሻልን አስከትሎ ቢሆን ኖሮ ምናልባት የተማሪው ንቅናቄ ሥር ነቀል ባህሪ እንዳይኖረው ይረዳ ነበር ብዬ አስባለሁ ።

ከሁሉም በላይ ግን ከዚህ የጸሀፌ ትዕዛዝም ሆነ ከሳቸው በኋላ ከመጡት የለውጥ ሐዋርያት ህልም ወደ ቅዠት መቀየር እኔ በግሌ የተማርኩት ነገር ቢኖር፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ገባር ጫንቃዬን ከበደኝ፣ መሸከም አልቻልኩም፣ “እኔም በሰብአዊነቴ ከፈጣሪዬ ጋር የምጋራቸው የማይነኩ መብቶች አሉኝ” ብሎ እምቢኝ! አሻፈረኝ! እስካላለ ድረስ፣ ሕልመኞች እርስ በርስ ይተላለቃሉ፣ ሃገሪቱም በኋላ ማርሽ ቁልቁል ትወርዳለች ። ትልቁ ችግር ሆኖ የተሰማኝ፣ ኢትዮጵያ ዜጎች አልነበሯትም፣ ዛሬም የሏትም፣ ወደፊት ግን ያለዜጋ እንደ ሃገር መቀጠል የማትችልበት መስቀለኛ መንገድ ላይ እየደረሰች ይመስለኛል ። ወይ ገባሮቿ ተነስተው ዜግነታቸውን ይጠይቃሉ፣ አልያም፣ የሞት/ሽረት ሚዛን ላይ እንዳቃሰተች የወሮበሎች የጦር አውድማ ትሆናለች ። ወንድሞቼ! እህቶቼ! ገባሮቿ ዜግነታቸውን እንዲጠይቁ የሚረዳቸውን ሁሉ ለማድረግ አንስነፍ ። እንጻፍ፣ እንግጠም፣ እንቀኝ፣ እንሸልል፣ እንተውን፣ እናጥና፣ ከሁሉም በላይ ግን ሁላችንም የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች በመሆናችን እንከባብር፣ እንመካከር፣ እንደማመጥ፣ እንተማመን ።

በየኤርትራ ‹‹ጉዳይ›› መጽሃፍ ውስጥ በጥልቅ የተዋወቅናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድን በ “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” ገጾች ውስጥ ይበልጥ እንተዋወቃቸዋለን ። ለምሳሌ፣ መስከረም 6 ቀን 1947 አም ከ24 አመታት የከንፈር ጓደኛቸው ከማድሟዜል ኮሌት ቫላድ ጋር በወንድማቸው ቤት የጋብቻ ቃል ኪዳን ሲያስሩ፣ እንደ አባት ሆነው ያሳደጓቸው ወንድማችው አቶ መኮንን ሀብተወልድ አልተገኙም ። ወንድማቸው ለምን እንዳልተገኙም ሲጠይቁ ከአቶ አካለ ወርቅ የተሰጣቸው መልስ “ሁለት ፈረንጆች ሲጋቡ እኛ ምን እናደርጋለን እያለ ሲቀልድ ነበር” የሚል ነው ። በዚህ ይጣሏቸዋል ቢያንስ ቅር ይሰኛሉ ብዬ ስጠብቅ “በማግስቱ ጠዋት እኔ ቤተመንግስት ስገባ፣ አቶ መኮንን ሲወጣ አገኘሁት ። ከሰላምታ በስተቀር እሱም ጋብቻዬ በመፈፀሙ እንኳን ደስ አለህ አላለኝም፣ እኔም ለምን ሳትመጣ ቀረህ ብዬ አልጠየኩትም” ይሉናል ። ይህ እንግዲህ ከዛሬ 57 አመታት በፊት ነው ። እስቲ ከኛው ዘመን የቤተሰብ ግንኙነት ጋር አስተያዩት? በመከባበርና ነፃነት ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነት እንደነበራቸው ነው የምንገነዘበው ። “ሥራ በዝቶበት ይሆናል፣ ፈረንጅ በማግባቴ ስላልተደሰተ ይሆናል” ወዘተ ብለው ጸሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ማሰላሰላቸው አይቀርም ። ሆኖም የወንድማቸውን ውሳኔ ተቀብለው በፍቅር ቀጥለዋል ። ድንቅ ነው ። ልንማርበትም ይገባል ። እህታችን አንድ ነገር ብታደርግ፣ ያን ያደረገችበት 10ሺህ ምክንያት ሊኖራት ይችላል ። እኛ ከገመትነው ውጪ ። ለዚያ የሚገባውን ክብደት መስጠት እንጀምር ። ህይወታችንንም ከመወሳሰብ ያድነዋል ። አክሊሉ ሀብተወልድ እንኳ ከአመታት በኋላ “…ወደ ኋላ ተመልሼ ሳሰላስል፣ … የእኔ ጋብቻ ሲፈጸም አቶ መኮንን ያልመጣበት ዋናው ምክንያት፣ ጸሀፊ ትዕዛዝ [ወልደ ጊዮርጊስ] `ምስክሬና ሚዜዬ በመሆናቸው፣ አብሮ ለመገኘት ባለመፈለጉ መሆን አለበት…”ገፅ 722 ይሉናል ።

ከአውሮፓ ጉብኝት መልስ፣ ኅዳር 27 ቀን 1947 አም ወልደ ጊዮርጊስ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ከመኮንን ሀብተወልድ ጋር የሚለያዩበት መድረክ፣ የመጽሀፉ ኤፒክ ድራማ ሆኖ ታይቶኛል ። የኢትዮጵያ ተውኔት አባት የነበረውን ፀጋዬን የተካ ባለቅኔ ቢገኝ፣ በመድረክ ላይ የማይጠገብ ድንቅ ሥራ ይወጣዋል ። በወልደ ጊዮርጊስ እንግዳ መቀበያ ክፍል ሁለቱ ጓደኛሞች
ሲወያዩ፣ ጸሀፌ ትዕዛዝ እንዲህ አሉ፣ “አንተ እኮ ጃንሆይን እንደ መለኮት እንጂ፣ እንደ ሰው አታያቸውም ። እንደ ሰው ጥሩ የሚሠሩት አለ ። እንደ ሰው የሚያበላሹትና የሚጎዱት አለ ። እኛ በቅን ስናገለግላቸውና ስንረዳቸው፣ እንዳይሳሳቱ መጠበቅና፣ የሚያደርጓቸውንም ስሕተቶች እንዲያርሙ ከመናገርና ከማስረዳት መቆጠብ የለብንም ። በዛሬው ሰአት አንተንና እኔን የሚለያየን ትልቁ ነገር፣ በዚህ በጃንሆይ ጉዳይ ነው” ይሏቸዋል ። መኮንንም ሲመልሱላቸው “አንተንና እኔን ያቀራረበንና እንደ ወንድማማች ሆነን ያስተባበረን ጃንሆይን ይዘን፣ የጃንሆይን ዕምነትና ድጋፍ አግኝተን፣ ወገናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሳፍንት አገዛዝ ለማላቀቅ እንችላለን ብለን ነው ። በዚህ መሠረት … ሁሉንም ባይሆን ብዙዎቹን አሸንፈናል… ደግሞስ አንተ ለአገራችን መሻሻል ያለህ ሃሳብ ከእሳቸው የፈጠነና ከእሳቸው የተሻለ ሆኖ፣ እሳቸው እንቅፋት ሆነው እንዳትሠራ ያደረጉህ መቼ ነው?...እንደ ኢትዮጵያ በመሰለው አገር በመሪና በአገልጋይ መካከል ሙግት ሲፈጠር፣ ፍጻሜው ጠብ ነው ። ጠብ ሲደርስ ደግሞ አሸናፊው መሪው ነው ። ተሸናፊው አገልጋይ ደግሞ መጨረሻው የትም ወድቆ መቅረት ነው ።… ለአንተና እኔ ዋስትናችን ጃንሆይ ብቻ ናቸው”4 ገፅ 727 ብለው ይሞግቱዋቸዋል ። እንደ ልማዳቸው እራት እንኳ አብረው ሳይበሉ ይለያያሉ ። ከመኮንን የግል ማህደር ነው ደራሲው ይህን የሚያካፍሉን ።

ይህ ቀን እንደሚመጣ አስቀድመው የተነበዩት በወቅቱ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ይልማ ዴሬሣ` ናቸው ።እኤአ መስከረም 1971 አም ደራሲው ለአሥር ቀናት ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ጋር ፓሪስ ላይ በሰነበቱባቸው ጊዜያቶች ነው የይልማን ትንቢት ያጫወቷቸው ። አክሊሉ እንዲህ ይላሉ “ወዳጄ ይልማዴሬሣ … ጸሐፌ ትዕዛዝ ከመሻራቸው አንድ አመት በፊት፣ በዋሽንግተን ተገናኝተን ትእየበላን ሰንጨዋወት…ስማ አክሊሉ ለኝ…እንደምታውቀው እነዚ ን ሁለት ሰዎች በሥልጣን በየደረጃው እያሳደጉ እንዲስማሙና እየተደጋገፉ ጃንሆይን የሚጠቅም አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጓቸው ራሳቸው ጃንሆይ ናቸው ። ወደፊትም አጣልተው የሚለያዩዋቸው ጃንሆይ ራሳቸው ናቸው ። በመጨረሻም፣ ከሁለቱ መካከል የሚያምኑትን አስቀርተው፣ የሚጠረጥሩትን ያባርራሉ ። ይህንንም ስል፣ ታማኝ አድርገው የሚያስቀሯቸው ያንተን ወንድም ሲሆን፣ ተጠርጣሪውና ተጠቂው ወልደጊዮርጊስ ይሆናሉ ማለቴ ነው” ገፅ 780 ይሉናል ። መጽሃፉም ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ተሽረው ግንቦት 6 ቀን 1947 አም ወደ አርሲ መንገድ ሲጀምሩ ይገባደዳል ። አንባብያን ሁሉ በሐዘን እንሸኛቸዋለን ። ልብ የሚያንጠለጥል ድራማ ነው።
ለማጠቃለል፣ ይህን “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት” ታሪክ፣ በዚህ በቀረበበት ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ለዛ፣ ከአምባሳደር ዘውዴ በቀር ማንም ማቅረብ አይቻለውም ነበር ። ከሃርቫርድ ወይም ኦክስፎርድ ዱክትርና በማግኘትም እንኳ ሊደረስበት የሚቻል አይመስለኝም ። ከንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ፀሃፊና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ላይ ቅሬታ ከነበራቸው አባት መወለዳቸው፣ የቤተመንግስት ዘጋቢ በመሆን በጋዜጠኝነት በመሥራታቸው፣ ለመኮንንና አክሊሉ ሀብተወልድ የነበራቸው ቤተኝነት፣ ከቤተ መንግስቱ ባለሟሎች ጋር የነበራቸው ቅርበት፣ ከጣሊያንና ፈረንሳይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከነአልዲሞሮ ጋር የነበራቸው ጓደኝነት፣ ከሁሉም በላይ ግን በኢትዮጵያ ጥናት ውስጥ ሁሌም መንምኖ የሚገኘው ለሥራ ታታሪ የሆነው ሥነ ምግባራቸው ለዚህ ልዩ ተልዕኮ አዘጋጅቷቸዋል ። በእኔ ዕምነት አምባሳደር ዘውዴ ተልዕኮውን በሚገባ ተወጥተውታል።
በመጨረሻ፣ አምባሳደር ዘውዴ ይህን ሲያዩት የሚከብድ፣ ሲይዙት የማይጠገብ እጅግ አድካሚ የነበረ ታላቅ ሥራ፣ ከዕድሜ፣ ከበሽታ፣ ከብቸኝነት ጋር እየታገሉ የኢትዮጵያችን ሥልጣኔ ፀሃይ ከመጥለቁ አንድ ሰአት አስቀድመው ደርሰው፤ የታሪክ ማዕዱ ላይ የተራረፈውን እየተቃመስን ቀስ ብለን ማዝገም እንድንችል በመጨነቅ ፣ አይዞን ላሉን ታላቅ ሰው ክፍያችን ምን ይሆን? ውለታ መላሽ ያድርገን ከማለት በቀር የምጨምረው የለኝም። አመሰግናለሁ። 


 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethioreaders.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
zenebe [1046 days ago.]
 Very good book review.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com